Logo
EBC
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቪዛ ኩባንያ ጋር በመተባበር አዲስ ዓለም አቀፍ የክፍያ ካርድ ይፋ አደረጉ
*************

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዓለም አቀፉ ቪዛ ኩባንያ ጋር በመተባበር፣ ደንበኞች በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነው በቀላሉ ግብይት እንዲፈጽሙ የሚያስችል አዲስ የተቀናጀ ዓለም አቀፍ የክፍያ ካርድ በይፋ አስጀምረዋል።

ይህ አዲስ የክፍያ ካርድ በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ“ሸባ ማይልስ” አባላት የሆኑ መንገደኞች በሚደርሱበት ማንኛውም የዓለም መዳረሻ ፈጣን፣ ቀላል እና አስተማማኝ ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ ዕድል ይሰጣቸዋል።

ካርዱ የዕለት ተዕለት ግብይቶችን ከማቅለሉ ባሻገር፣ ለአጠቃቀም እጅግ ቀላልና አስተማማኝ የደኅንነት ጥበቃ ሥርዓት ያለው መሆኑ ተገልጿል። በተጨማሪም የሦስቱንም ተቋማት ዓርማና ምልክት በአንድ ላይ የያዘ ነው።

አዲሱ ዓለም አቀፍ የግብይት ካርድ ለደንበኞች ልዩ ልዩ ሽልማቶችንና ጥቅማጥቅሞችን የሚያስገኝ ሲሆን፣ ለአዲስም ሆነ ለነባር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞች ክፍት መሆኑ ተረጋግጧል።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በየጉዟቸው የሚያደርጉት ግብይት ተጠራቅሞ ወደ ጉዞ ዕድል (ማይልስ) የሚቀየርላቸው ሲሆን፣ ካርዱን በሽያጭ ማሽን (POS) ወይም በኢ-ኮሜርስ (e-commerce) አማካኝነት ለኦንላይን ግብይት በሚጠቀሙበት ወቅትም ለተጨማሪ ሽልማቶች ያላቸውን ዕጩነት በከፍተኛ ደረጃ ያሰፋላቸዋል።

ይህ አገልግሎት የሮያሊቲ (ታማኝ) ደንበኞችን ክብርና ጥቅማጥቅም ከመጠበቁ በላይ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞቹን ዘመናዊ ፍላጎት ለማሟላት ለሚያደርገው ጉዞ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተጠቅሷል።

በሌላ በኩልbox እነዚህ ሁለቱ አንጋፋ ሀገራዊ ተቋማት ከዓለም አቀፉ ቪዛ ካርድ ጋር በጋራ ለመሥራት መፈራረማቸው ተቀባይነታቸውንና የገበያ ድርሻቸውን ይበልጥ የሚያሳድግላቸው ሲሆን፣ ለቪዛ ካርድም ቢሆን በማደግ ላይ ወዳሉ ሀገራት ገበያ ለመግባትና ተደራሽነቱን ለማስፋት ምቹ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርለት ተገልጿል።

በሳራ ሳህለሥላሴ
#commercialbankofethiopia #ethiopianairlines #visacard #cobrandedcard #shebamiles #digitalpayment #ethiopianbroadcastingcorporation

10 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.