Logo
Getu Temesgen
በጎቲያ ካፕ የተሳተፉ 20 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ታዳጊ ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በስዊድን መሰወራቸው ተረጋገጠ
#ethiopia | በስዊድን ጎተንበርግ ከተማ በተካሄደው የ2026 የ«ጎቲያ ካፕ» ዓለም አቀፍ የታዳጊዎች እግር ኳስ ውድድር ላይ የተሳተፉ 20 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ታዳጊ ተጫዋቾችና ቢያንስ አንድ የቡድን አመራር አባል ከውድድሩ በኋላ መሰወራቸውን የስዊድን ፖሊስ አረጋግጧል።

በስዊድን ፖሊስ መረጃ መሠረት፣ ቡድኑ ያረፈበትን ትምህርት ቤት ለቆ ያለማሳወቅ እንደወጣ ከታወቀ በኋላ ለፖሊስ ሪፖርት ተደርጓል። ፖሊስ እስካሁን የወንጀል፣ የሰው ዝውውር ወይም የግዳጅ ማስጠፋት ምልክት እንዳልተገኘ ገልጾ፣ ድርጊቱ በራሳቸው ፈቃድ የተፈጸመ እንደሚመስል አስታውቋል።

የጎቲያ ካፕ አዘጋጆች በበኩላቸው ከቡድኑ አንድ አመራር ጋር ግንኙነት እንዳደረጉ ገልጸው፣ ተጫዋቾቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘታቸውንና በደህና መሆናቸውን ቢናገርም፣ አሁን የሚገኙበት ቦታ እንደማይታወቅ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በኩል የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ አብርሃም ገብረማሪያም፣ የተሰራጨው መረጃ እውነት መሆኑን አረጋግጠው፣ ወደ ስዊድን የሄደው ቡድን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ወክሎ የተላከ ሳይሆን በግል አደረጃጀት የተሰባሰበ ቡድን መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መግለጫ እንደሚያወጣ አስታውቋል።

«ጎቲያ ካፕ» በዓለም ላይ ትልቁ የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር ሲሆን፣ በ2026 ውድድሩ ከ78 አገራት የመጡ ከ45,000 በላይ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ተሳትፈዋል።
#ethiopia #gothiacup #sweden #sportsnews #getutemesgen #getunews

9 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.