Logo
Getu Temesgen
የከንቲባ ቀውስ ያጋጠማት አፍሪካዊት ከተማ
#ethiopia | እ.ኤ.አ ከ2016 ጀምሮ በአፍሪካ በኢኮኖሚዋ ትልቅ ቦታ የምትይዘው ከተማዋ ዘጠኝ ከንቲባዎች ተፈራርቀውባታል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የከተማዋ የፖለቲካ አመራር ችግር ሀገራዊና አህጉራዊ አንድምታ እናዳለውም እየተነገረ ይገኛል፡፡

የደቡብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማዕከል የሆነችው የጆሃንስበርግ ከተማ ከ2016 ጀምሮ ባሉት ዓመታት ውስጥ ዘጠኝ ከንቲባዎች እንዳሻት ቀያይራለች፡፡

ይህ ቀውስም ነዋሪዎች እንደኃይል፣ ውሃና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን በአግባቡ እንዳያገኙ በማድረግ ችግር ውስጥ እየከተታቸው ይገኛል ተብሏል፡፡

በከፋ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የፍጆታ ዋጋ መጨመር እና በፖለቲካዊ ሽኩቻ ጆሃንስበርግ በየወቅቱ የከንቲባ ቀውስ እንዲያጋጥሟት ሆኗል።

በሶዌቶ ዱቤ ከተማ ውስጥ የብላክ ኮንሸስ ንቅናቄ አቀንቃኝ እና ለረጅም ጊዜ ነዋሪ የሆኑት ምፖትሰንግ ጃይረስ እንደሚሉት፤ ከሆነ የከተማው ምክር ቤት አባላት አለመታወቃቸውና ከዜጎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጣቸው የአገልግሎት አሰጣጥ መዳከም ለከንቲባዎቹ መቀያየር ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ይገልጻሉ።

በሶዌቶ የሀገሬው ተወላጅና በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት ማሴቻባ ኖናያና በበኩላቸው፤ በአመራሩ መካከል ያለው ይህ ልዩነት በከተማዋ ውስጥ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር እየፈጠረ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

አክለውም በተደጋጋሚ እየተከሰተ ስላለው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እና የታሪፍ ጭማሪ እንደ ሻማ፣ የፀሐይ ኃይልና ጋዝ ያሉ አማራጮችን እየተጠቀሙ ስለመሆኑ ገልጸው፤ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ዜጎች እነዚህ አማራጮች እንደሌላቸው አውስተዋል።

እ.ኤ.አ ነሀሴ 16 ቀን 2024 በይፋ ቃለ መሃላ የፈጸሙት የወቅቱ ከንቲባ ዳዳ ሞሬሮ የካቤሎ ጉማንዳ ስልጣን መልቀቅ ተከትሎ በምትካቸው ጆሃንስበርግን ለማረጋጋት እና መሰረታዊ ተግባራትን ወደነበረበት ለመመለስ የታለሙ ስራዎችን ተግባራዊ አድርገዋል።

በኤሌክትሪክ በ12 ነጥብ 7 በመቶ፣ በውሃ እና በንፅህና አጠባበቅ በ13 ነጥብ 9 በመቶ እንዲሁም በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ ለማህበረሰቡ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ሊያባብሰው እንደሚችል ተነግሯል፡፡

በጆሃንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ተንታኝ ፕሮፌሰር ፓትሪክ ቦንድ በአካዳሚክ መጽሔት ጽሁፋቸው ላይ ይህንን ቀውስ በሰፊው አቅርበዋል።

"የከተማዋ ውድቀት ስር የሰደደ እና ኢ-ፍትሀዊነት የተንሰራፋበት ነው። አመራሩ ከተምሳሌታዊ ሪፎርም ወደ መዋቅራዊ ለውጥ እስኪሸጋገር ድረስ ድሃው ህዝብ ከፍተኛውን ዋጋ እየከፈለ ይቀጥላል" ብለዋል።

ጆሃንስበርግ ወደ 2026 የማዘጋጃ ቤታዊ ምርጫ እያመራች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ጥያቄው ቀጣዩ ከንቲባ ማን ይሆናል የሚለው ብቻ አይደለምም ይላሉ።

የቀድሞ ዘጠኝ ከንቲባዎችን ውድቀት ያስከተሉት መዋቅራዊ ችግር ይሆን ወይስ የግል ብቃታቸው የሚለውም ነው።

አሁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ከመንግስታቸው አስተማማኝ የኤሌክትሪክ፣ የንፁህ ውሃ እና የመሠረታዊ አገልግሎቶችን በመጠባበቅ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡ #gazette_plus

11 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.