Logo
EBC
የአፋር ሕዝብ የህልውና ትግል እና የአሰብ እውነታ
***************

ከዳህላክ እና ምጽዋ ጀምሮ እስከ ታጁራ ድረስ ከአንድ ሺህ ኪሎሜትር በላይ በተዘረጋው የቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ በመሃል ሌላ ማኅበረሰብ ሳይኖር ብቸኛ ነዋሪ የሆነው የአፋር ሕዝብ፣ ከእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ እና ከተፈጥሮ መኖሪያ ምድሩ የተነጠለው በፍላጎቱ አልነበረም።

ይህ ሰፊ የባሕር ጠረፍ የሕዝቡ ተፈጥሯዊ መተንፈሻ እና የህልውናው መሠረት ቢሆንም፣ በፖለቲካዊ ሤራ ከባሕሩ እና ከወንድሞቹ እንዲገነጠል መደረጉን ኢቢሲ በጉዳዩ ዙሪያ ያሰናዳው ዘጋቢ ፊልም ይገልጻል።

በወቅቱ የአፋር ሕዝብ መሪ የነበሩት ሱልጣን አሊሚራህ ሀንፈሬ በጊዜው የተደረገውን አፋርን ለሁለት ቆርጦ የመገንጠል ድርጊት አጥብቀው ተቃውመውት ነበር።

ሱልጣኑ የኤርትራ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብት አለው በሚል የአፋርን ሕዝብ ለሁለት በከፈለው የኤርትራ ሪፈረንደም ላይ የአፋር ሕዝብ ጥያቄ እንዳለው ጠቅሰው፣ "አፋር ከኢትዮጵያ ጋር ነው የሚገናኘው" በማለት በግልጽ ሞግተዋል።

የአፋር ቋንቋ ባህልና ታሪክ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሀቢብ መሐመድ እንደሚሉት፣ ሱልጣን አሊሚራህ ሀንፈሬ በወቅቱ አፋርን ለሁለት ከፍሎ የመገንጠልን ድርጊት በጽኑ ተቃውመዋል።

የአፋሮች መኖሪያ የሆነው የአሰብ አካባቢ እንዳይለማ እና እንዲራቆት መደረጉን የሚጠቅሱት ሀቢብ መሐመድ፣ ይህ የተደረገው አፋር ኢትዮጵያዊነቱን ስለሚያውቅ አንድ ቀን መመለሱ አይቀርም ብለው ስለሚፈሩ እንደሆነ ይናገራሉ።

የቀድሞ የአሰብ ከተማ ምክትል ከንቲባ አሊ ኢሳ መሐመድ፣ ሱልጣኑ "ዴሞክራሲ ከሆነ ኤርትራ ላለው የአፋር ሕዝብ ለምን የመምረጥ ዕድል አይሰጠውም?" ብለው ሲናገሩ፤ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ስብሰባውን ረግጠው ወጥተው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ይህ የዴሞክራሲ ጥያቄ ምላሽ በማጣቱ ሱልጣኑ ሀገር ለቅቀው እንዲወጡ ተገደዱ፤ አፋርም ሳይወድ በግድ ተከፈለ።

ኤርትራ ነጻ ሀገር ከሆነች በኋላ በቀይ ባሕር አፋሮች ላይ የደረሰው ሰቆቃ ዋነኛ ዓላማ ሕዝቡን ከተፈጥሮ ምድሩ ማላቀቅ እንደነበር አስተያየት ሰጪዎቹ ይናገራሉ።

አቶ ሀቢብ መሐመድ እንዳብራሩት፣ ኢሳይያስ አፈወርቂ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የነበራቸው ድብቅ አጀንዳ አፋርን ከቀይ ባሕር ጠረፍ ሙሉ በሙሉ ማጽዳት ነበር።

የተፈለገው መሬቱ እንጂ ሕዝቡ ባለመሆኑ ማፈናቀል፣ ግድያ እና ንብረት መውረስ ስልታዊ በሆነ መንገድ ተፈጽሟል።

ከማፈናቀል ባለፈ ወጣቶችን ከ12ኛ ክፍል በኋላ ወደ ሳዋ ወታደራዊ ካምፕ በግድ በመውሰድ፣ ባህላቸውን እንዲረሱ የማድረግ የማንነት ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል።

የአፋር ቀይ ባሕር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር ኢብራሂም ሀሩን እንደሚሉት፣ ሳዋ የባህል እና የቋንቋ መጥፊያ ሲሆን፤ ሕዝቡ ሀገሩን ለቅቆ እንዲሄድ፣ የቀረው ደግሞ ቋንቋ እና ባህሉን እንዲተው ተገድዷል።

አሊ ኢሳ መሐመድ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በአካባቢው የነበረው የአፋር ሕዝብ ተፈጥሯዊ የዓሣ ማጥመድ ሥራ በማፊያዎች እና በሕገወጥ መረቦች እንዲወድም ተደርጓል።

ዓሣ የሚኖርበትን እና ኮራል ያለበትን አካባቢ ጠራርጎ በሚወስድ መረብ ባሕሩ እንዲቀየር ከመደረጉም በላይ፣ ማፊያዎች ሚሊዮን ዶላሮች እየተቀበሉ መርዛማ ቆሻሻዎችን ባሕሩ ውስጥ እንዲጥሉ ተደርጓል።

አፋሮች በተፈጥሮ ሀብታቸው እንዳይሠሩ መከልከላቸው እና ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለእስር መዳረጋቸውም የዚሁ ግፍ አካል ነው።

የቀድሞው የአሰብ ምክትል ከንቲባ ለ13 ዓመታት ያለ ፍርድ መታሰራቸውን ገልጸው፣ ጉዳያቸው ለባህላዊው የአፋር ፍርድ (መድዓ) እንዳይቀርብ መከልከሉም የሕዝቡን ሕግ እና ባህል ለማጥፋት እንደሆነ አብራርተዋል።

የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ሌ/ጄኔራል ጻድቃን ገ/ተንሣይ እንዳብራሩት፣ የባህላዊው አውሳ ሱልጣኔት ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ ማዕከል ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።

ምንም እንኳን አርቲፊሻል ድንበሮች ተሰምረው ሕዝቡን ከባሕሩ ቢያርቁትም፣ የአፋር ሕዝብ ማዕከል ምንጊዜም ኢትዮጵያ መሆኗን ጄኔራል ጻድቃን አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህን እውነት ሲያጠናክሩ፣ የኤርትራም ሆነ የጅቡቲ አፋሮች በውክልና መጥተው ባህላዊ መሪያቸውን የሚመርጡት አሳይታ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአውሳ ሱልጣኔት ማዕከሉ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን አስምረውበታል።

ከሰላሳ ዓመታት ዝምታ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሰብን ጉዳይ ማንሳታቸው በአፋር ሕዝብ ዘንድ የፈጠረውን ወደር የለሽ ደስታ በተመለከተ ሀቢብ መሐመድ ሲገልጹ፣ "የአፋር ስሜቱ ገንፍሎ ወጥቷል፤ ከልክ በላይም ተደስቷል" ብለዋል።

ጥያቄያችን የዴሞክራሲ አይደለም የሚሉት የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር ኢብራሂም ሀሩን፣ ምክንያቱንም ሲያስረዱ "የአፋር ሕዝብ ይኖራል ወይስ አይኖርም?" የሚል የሕልውና ትግል ውስጥ በመገባቱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የተነጠቀውን ጠረፍ በመመለስ የአፋርን አንድነት ማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን እንዲሁም ታሪክን ከመደለዝ መታደግ የአፋር ሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑን ሊቀመንበሩ ያብራራሉ።

የቀይ ባሕር ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ከማንም በላይ ጥቅሙ የአፋር ሕዝብ መሆኑን የጠቀሱት ሀቢብ መሐመድ፣ ባሕሩ ወደ ባለቤቱ እንዲመለስ አፋር አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በለሚ ታደሰ
#ethiopia #afar #seaaccess #seaport #redsea #assab #hornofafrica #ebc

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.