Logo
EBC
የታሪክ ስህተቶችን በማረም ለነገይቱ ጠንካራ ኢትዮጵያ መሠረት የሚጥለው ሀገራዊ ምክክር
*******************

ታሪካዊው የሀገራዊ ምክክር ዋና ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ እና ዘላቂ ውጤት እንዲያመጣ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስተላለፉት መልዕክት ለውይይቱ መነሻ የሚሆን ጠንካራ እሳቤን ይዟል።

ይህ መልዕክት የኢትዮጵያ የትናንት ሕመም፣ የዛሬ ፈተና እና የነገ ተስፋ በግልጽ የተንጸባረቀበት ነው።

የውስጥ ድክመት እና የውጭ ጣልቃ ገብነት አንደምታ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገራችን ውስጣዊ ክፍተቶች ምክንያት የሚመጡ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን እና የጂኦፖለቲካ አደጋዎችን በምሳሌ አስረድተዋል።

የዚህ መልዕክት ትልቁ አንደምታ ግልጽ ነው፤ እኛ እርስ በርሳችን በውስጥ ጉዳዮቻችን ስንጨቃጨቅ እና ስንወዛገብ፣ የውጭ ኃይሎች መዳከማችንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የራሳቸውን ፍላጎትና ጥቅም በላያችን ላይ ይጭናሉ።

ይህን እውነት ለማሳየትም ታሪካዊ ስህተቶቻችንን አስታውሰዋል። ቀደም ባሉ ጊዜያት ልዩነቶቻችንን በውይይት መፍታት አለመቻላችን እና ውስጣዊ አንድነታችን መላላቱ ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን እንድታጣ አድርጓታል።

ይህም በታሪክ "የጂኦግራፊ እስረኛ" እንድንሆን አድርጎናል። የዚህ ታሪካዊ እውነት አንደምታ፣ የውስጥ መከፋፈል የአንድ ትውልድ ስህተት ብቻ ሳይሆን የብዙ ትውልዶችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚያጨልም ታሪካዊ ኪሳራ ማስከተሉን ሊያስተምረን ይገባል የሚል ነው።

"እኔ ብቻ" ከሚል ግትርነት ወደ መደማመጥ ባህል

የምክክሩ ስኬት የሚጀምረው ከአስተሳሰብ ለውጥ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ "እኔ ያልኩት ብቻ" በሚል ግትርነት የውይይት ባህልን የመቁረጥ አደገኛ አካሄድ መታረም እንዳለበት አሳስበዋል።

መደማመጥ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማስረዳትም የሀገራችንን ሁለት ድንቅ አባበሎች ጠቅሰዋል።

"መልካም ንግግር ከመልካም አልጋ በተሻለ ያሳርፋል" የሚለው የኦሮሞ አባቶች ይትበሃል እና "በአንድ ወገን ቆመህ የሌላውን ችግር መረዳት አትችልምና፣ ተነስተህ ሂድና አድምጥ" የሚለው የአፋሮች ጥልቅ ምክር የዚህ ማሳያ ናቸው።

የነዚህ አባባሎች አንደምታ ቀላልና ግልጽ ነው፤ ሰላም እና መግባባት የሚመጣው በጉልበት ሳይሆን በሃሳብ ልዕልና ነው።

እውነተኛ መግባባት የሚፈጠረው ደግሞ ከራሳችን ጠባብ አጥር ወጥተን የሌላውን ወገን ስሜት፣ ሃሳብ እና ስጋት ለመረዳት ስንሞክር ብቻ ነው።

በአሁኑ ወቅት የተሰበሰቡት 4 ሺህ ተሳታፊዎች ዋነኛ ሥራም ይህን የመደማመጥ ባህል በማዳበር ለሀገራችን ዘላቂ ሕገ-መንግሥታዊ ዋስትና ያለው ሥራ መሥራት ነው።

የውሸት ፕሮፓጋንዳ እና የሀገር ሕልውና

ሌላው ትልቁ መልዕክት፣ ተሳታፊዎች በውሸት ፕሮፓጋንዳዎች እንዳይዘናጉ የቀረበው አደራ ነው። ይህንንም "ቀፎዋን የጣለች ንብ፣ ማር አትሰጥም" በሚል ምሳሌ አስገንዝበዋል።

ሀገር ከሌለች ግለሰባዊም ሆነ ቡድናዊ ሕልውና ሊኖር አይችልም። ማር መሥራት የሚቻለው ቀፎው ሲኖር እና ንቦቹ በጋራ ሲሠሩ ብቻ ነው።

በመሆኑም በሀሰተኛ መረጃዎች እና አሉባልታዎች ተታልለን የጋራ ቀፎአችን የሆነችውን ሀገራችንን ማፍረስ፣ ከሁለት ያጣ እንደሚያደርገን መረዳት ያስፈልጋል።

ወደ አዲሱ የሰላም ሞዴል

ይህ ታሪካዊ የምክክር መድረክ እርስ በርስ በመደማመጥ አሁን ያለውን የዜሮ ድምር ፖለቲካ በምክክር እና መደማመጥ ላይ ወደተመሠረተ ዘላቂ ሰላም እና ልማት ለመለወጥ የተዘጋጀ ትልቅ በር ነው።

የፍትህ እና የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ቀንድ እና ለመላው አህጉር አርአያ የሚሆን የሰላም ሞዴል የማድረግ ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አሁን በተመካካሪዎቹ እጅ ላይ ይገኛል።

በለሚ ታደሰ
#ethiopia #pmabiyahmed #nationaldialogue #peacebuilding #reconciliation #ebc

24 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.