Logo
EBC
በውይይት የምትጸና ሀገር፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለቀጣዩ ትውልድ የተሰናዳ የሰላም ቅርስ
**************

የኢትዮጵያን የቆዩ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከጠመንጃ ድምፅ ይልቅ የሰለጠነ ውይይትና ምክክር ብቸኛውና ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ አማራጭ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም።

"በውይይት ብቻ የምትጸና ሀገር" የሚለውን እሳቤ እንደ መርህ በማንገብ ወደ ሥራ የገባውና በየደረጃው የሕዝብ አስተያየትና አጀንዳ በማሰባሰብ ከመጨረሻው ምዕራፍ የደረሰው ሀገራዊ ምክክር ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ ለሰለጠነ ፖለቲካዊ ባህል ግንባታ እና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ምስረታ ዋስትና የሚሆን ታሪካዊ ሁነት መሆኑ ተመላክቷል።

ይህንን ሀገራዊ ምክክር ከሌሎች የቀደሙ ውይይቶችና ንግግሮች ልዩ የሚያደርገው አንዱና ዋናው ነገር ከዚህ ቀደም በፖለቲካ ተዋናዮች ብቻ ይታጠር የነበረውን አሠራር በማስፋት በየደረጃው የሚገኘውን ሕዝብ ከሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ያሳተፈ መሆኑ ነው።

ሂደቱ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከታዋቂ ግለሰቦች አልፎ አርሶ አደሩን፣ ወጣቱን፣ ሴቶችን፣ የሃይማኖትና የሀገር ሽማግሌዎችን እንዲሁም ልዩ ትኩረት የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሁሉ ያካተተ ሲሆን፤ እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ውይይትና የአጀንዳ ቀረጻ ሂደት በየጊዜው ለሕዝብ ይፋ መደረጉ የሂደቱን ግልጸኝነትና የጋራ አመኔታ ያረጋግጣል።

ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ አሳታፊነትንና አካታችነትን ግንባር ቀደም መርሆቹ በማድረግ ከቀዳሚ የሕብረተሰብ ክፍል ጀምሮ በክልል ደረጃ የተዋቀሩ ማኅበራትን፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና የሲቪክ ማኅበራትን በማሳተፍ የምክክሩ ባለቤት ሕዝብና ተቋማት እንዲሆኑ ጠንካራ መሠረት ጥሏል።

ታሪክ እንደሚያስተምረው በውስጣዊ ግጭትና በፖለቲካ ልዩነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያለፉ እንደ ቱኒዚያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኮሎምቢያ ያሉ ሀገራት ከመፈራረስ አደጋ ለመዳን የተጠቀሙበት ዋናው መሣሪያ "ሀገራዊ ምክክር" መሆኑ ይታወቃል።

የቱኒዚያው "ሀገራዊ የውይይት ስብስብ" ሀገሪቱን ከእርስ በርስ ጦርነት ታድጎ ለኖቤል ሰላም ሽልማት ያበቃ ሲሆን፣ የደቡብ አፍሪካው የ"እውነትና እርቅ ኮሚሽን" ያለፈውን በደል በይቅርታ በመሻገር ለአዲሲቷ ዲሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪካ መሠረት ጥሏል።

እንዲሁም ለአምስት አስርት ዓመታት የዘለቀውን የኮሎምቢያ ግጭት በድርድር መፍታት መቻሉ ምክክር የረጅም ጊዜ ትዕግስትና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ የጥንካሬ መገለጫ መሆኑንና ሰላም የውይይት እንጂ የግዳጅ ውጤት አለመሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተሞክሮነት አሳይቷል።

በአንጻሩ ምክክርን ችላ ያሉና የልዩነት ድምፆችን ያፈኑ ሀገራት በቀላሉ ወደ ደካማ መንግሥትነትና መፈራረስ እንደሚያመሩ የታየ በመሆኑ፣ ሀገራዊ ምክክር የሰላም አማራጭ ብቻ ሳይሆን የህልውና ዋስትና መሆኑ ይነገራል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ውይይት ብቻ ሳይሆን ሀገራችን በታሪኳ ያሳለፈቻቸውን የተዛቡ ትርክቶች እና የፖለቲካ ቁርሾዎች በውይይት በመፍታት ለቀጣዩ ትውልድ ሰላማዊና የተረጋጋች ሀገርን ለማስረከብ የሚደረግ ታሪካዊ የይቅርታና የመግባባት ጉዞ ነው።

ይህ ሂደት ትውልዱ ከጥላቻ ፖለቲካ ወጥቶ በጋራ እሴቶች ላይ እንዲታነጽና የውይይት ባህልን እንዲያዳብር የሚያስችለው ሲሆን፣ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ጉልበቱን ለግጭት ሳይሆን ለፈጠራ፣ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታና ለሳይንሳዊ ዕድገት እንዲያውል ዕድል የሚፈጥር ነው።

በጥቅሉ በሕዝቦች መካከል የጋራ መግባባትን በመፍጠር የዜግነት ክብርን የሚያሳድገውና በጋራ ሕልም ዙሪያ የሚተጋ ትውልድ የሚቀርጸው ይህ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር፣ መላውን ሕዝብ ከክክፍል ወደ አንድነት፣ ከጥርጣሬ ወደ መተማመን እና ተስፋ የሚያሸጋግር ታላቅ ብሔራዊ ሁነት መሆኑ ተመላክቷል።

በብሌን ደምበሎ
#ethiopianbroadcastingcorporation #nationaldialogueethiopia #nationalconsultation #peaceandunity #inclusivedialogue

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.