Logo
EBC
የ5ቱ ዓመታት ገፆች፦ መደመር ያዋለዳቸው የገበታ ፕሮጀክቶች
**************

ታሪክ በየዘመኑ የራሱን ዐሻራ ጥሎ ያልፋል። ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ አንስቶ ወደ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዋዜማ ስንሸጋገር የተፃፉት የአምስቱ ዓመታት ገፆች ደግሞ፣ ኢትዮጵያ ድብቅ የተፈጥሮ ውበቷንና ፀዳሏን አውጥታ ለዓለም ያሳየችባቸው የውበት አብዮት ድርሳናት ናቸው።

ለዘመናት "የ13 ወር ፀጋ" በሚለው የቱሪዝም መሪ ቃል ብቻ ስትጠራ የነበረችው ሀገራችን፣ ዛሬ ከመፈክር ባለፈ "ምድረ ቀደምት" በሚለው ከፍታዋ ልክ በተጨባጭ በዓለም አቀፍ መድረክ ደምቃ እንድትታይ ያደረጋት አስደናቂ የታሪክ እጥፋት ተፈጥሯል። የዚህ ታላቅ ሀገራዊ ትራንስፎርሜሽን የጀርባ አጥንትና ሞተር ደግሞ ከመደመር እሳቤ የተወለዱት የ"ገበታ" ፕሮጀክቶች ናቸው።

የገበታ ፕሮጀክቶች “ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ” ተራ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች አይደሉም። ይልቁንም ሃብትን አስተባብሮ ከተፈጥሮ ፀጋዎች ጋር በማዋሀድ ኢትዮጵያን ወደ ተፈጥሯዊ የቱሪዝም መስህብነት የቀየሩና ከመደመር እሳቤ የፈለቁ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ትርክቶች ናቸው። የመደመር ትውልድ ሀገርን ማልማት ማለት የውጭ ዕርዳታን መጠበቅ ሳይሆን፣ የራስን እምቅ አቅም፣ የተፈጥሮ ውበትና ታሪክን ወደ ኢኮኖሚያዊ እሴት መቀየር መሆኑን በተግባር አሳይቶበታል።

ይህ የገበታ ጉዞ የተጀመረው በ"ገበታ ለሸገር" ሲሆን፣ ለዘመናት በቆሻሻ ተውጠው የነበሩ የከተማ ቦታዎችንና የተተው ተራራዎችን ወደ ምድር ገነት ቀይሯቸዋል። ጫካና ገደል የነበረው የእንጦጦ ተራራ ወደ ማራኪው "እንጦጦ ፓርክ" ሲቀየር፣ የአዲስ አበባን የልብ ትርታ ያደሰው "ወዳጅነት ፓርክ" እና ታሪክን ከተፈጥሮ ጋር ያዋሀደው ግዙፉ "አንድነት ፓርክ" የዚህ ስኬት በኩር ፍሬዎች ሆነዋል።

ይህ ስኬት በመዲናዋ ብቻ አልተገታም፤ የመደመር እሳቤ "ገበታ ለሀገር" በሚል አዲስ ሀገራዊ ንቅናቄ መላዋን ኢትዮጵያ አዳረሰ። ማራኪው የ"ወንጪ" ሐይቅ ከተፈጥሮ አቀማመጡ ጋር በተዋሀደ መልኩ በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ለቱሪዝም ክፍት ሆነ። የጣናን ሐይቅ ሞገድ የሚያማትረው የ"ጎርጎራ" ፕሮጀክት ታሪካዊቷን ከተማ ዳግም ሲያነቃ፣ በደቡብ ምዕራብ የሚገኘው "ኮይሻ" እና የታላቁ ሸለቆ ድንቅ ስጦታ የሆነው "ሀላላ ኬላ ሎጅ" እንዲሁም በጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ የተገነባው “ጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ” የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ውበትና የባህል ብዝኃነት ቁልጭ አድርገው አሳይተዋል።

በዚህ ያላቆመው የመደመር ትውልድ "ገበታ ለትውልድ" በማለት ሌላ ምዕራፍ ከፈተ። የደንዲ ሐይቅ፣ የጢስ አባይ ፏፏቴ፣ የጅማ ዞን ቦንጋ አካባቢ እና የሶፍ ኡመር ዋሻን ጨምሮ በርካታ ድንቅ የቱሪስት መዳረሻዎች በተፈጥሮ ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ በማያሳድር (eco-friendly) እና ከዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ጋር በተናበበ አኳኋን እየተገነቡ ይገኛሉ።

እነዚህ ሁሉ የገበታ ፕሮጀክቶች ስኬታማ ሊሆኑ የቻሉበት ትልቁ ምስጢር የሥራ ባህል ለውጥ ነው። ፕሮጀክቶቹ የተመሩት "ጥራትና ፍጥነት"ን ባማከለ ጽኑ መርህ ነው። ለዘመናት ሲንከባለሉና ሲጓተቱ የነበሩ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ልማድ በመስበር፣ የገበታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀት፣ በተቀመጠላቸው እጅግ አጭር ጊዜ እና ዓለም አቀፍ ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ ተጠናቅቀዋል። ፕሮጀክቶቹ ከተፈጥሮ ጋር የፈጠሩት አስደናቂ መስተጋብር ሳይነካ የአካባቢን ሥነ-ምህዳር በጠበቀ መልኩ የተከናወኑ በመሆናቸው፣ ሀገራችንን የዓለም ጎብኚዎች ተመራጭ መዳረሻ አድርገዋታል።

የገበታ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን እውነተኛ ፀዳል የገለጡ፣ የመደመር ትውልድ ሀገሩን በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ካርታ ላይ ቀዳሚ ለማድረግ ያለውን ብቃት፣ ፍጥነትና የፈጠራ ጥበብ ያረጋገጡ ሕያው ሐውልቶች ናቸው።

ኢትዮጵያም "ምድረ ቀደምት" መሆኗን በኩራት እያወጀች፣ የተፈጥሮና የሰው ልጅ ጥበብ የተዋሀደበትን አዲሱን ገፅታዋን ለዓለም እየገለጠች ትገኛለች።

በአጠቃላይ፣ ከስድስተኛው እስከ ሰባተኛው ምርጫ የተጓዝንባቸው የአምስቱ ዓመታት ገፆች፣ የኢትዮጵያ ውበት ከግጥምና ከዘፈን ወጥቶ መሬት የነካባቸው የክብር ዘመናት ናቸው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
#ethiopia #tourism #ecotourism #greentourism #sustainabletourism #ebc

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.