Logo
FastMereja
በምግብ ወለድ በሽታዎች በዓለም ላይ በየዓመቱ እስከ 1.5 ሚሊዮን ሕዝብ ይሞታል ተባለ!
#fastmereja I በዓለም ላይ በየዓመቱ ወደ 866 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በምግብ ወለድ በሽታዎች (Foodborne illnesses) የሚጠቁ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ እስከ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) አዲስ ያወጣው መረጃ አመለከተ።

ይህ አስደንጋጭ የወረርሽኝ ጫና በተለይ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን እና በማደግ ያሉ አገራትን በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቃ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን (EFDA) ከዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ጋር በመተባበር “ከምግብ ደህንነት ችግሮች ወደ መፍትሔዎች በሁሉም ቦታ ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ” በሚል መሪ ቃል በዛሬዉ እለት በስካይላይት ሆቴል ባዘጋጁት የዉይይት መድረክ ላይ ነው።

መድረኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ8ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ7ኛ ጊዜ የተከበረውን የዓለም የምግብ ደህንነት ቀንን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የደብሊውኤፍፒ (WFP) የሰፕላይ ቼይን ኃላፊ የሆኑት ክላራ ሲልቫ እንደገለፁት ፣ እነዚህ ቁጥሮች ዝም ብለው ቁጥር ብቻ ሳይሆኑ አስቸኳይ የድርጊት ጥሪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ድርጅታቸው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ለ3 ሚሊዮን ተጋላጭ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከ2026 እስከ 2030 ባለው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ምግብን ከውጭ ከማስገባት ይልቅ ወደ ሀገር ውስጥ ምርት ግዢ (Local Sourcing) ለማሸጋገር እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን በበኩሉ የምግብ ቁጥጥር ሥርዓቱን "ከቅድመ-ገበያ እስከ ድኅረ‐ገበያ" ለማዘመን በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ይፋ ያደረገ ሲሆን በተጨማሪም በኬላዎች ላይ ያለውን ቁጥጥር የሚያጠናክር ግዙፍና ዘመናዊ የላቦራቶሪ ኮምፕሌክስ ግንባታ ወደ ማጠናቀቂያው መድረሱ ተገልጿል።

እንዲሁም ማንኛውም ያልታወቀ ወይም ያልተረጋገጠ የምግብ ምርት ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ፣ ይዘቱና የአመራረት ሂደቱ በጥልቀት የሚገመገምበት ዘመናዊ የሰነድ ምዝገባ ሥርዓት ወደ ሥራ መግባቱን አስታዉቋል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሄራን ገርባ በመርሃ-ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፣ ይህንን የጥራት ማረጋገጫና የቁጥጥር ሥርዓት ወደ ክልሎች፣ በተለይም የተቀናጁ የግብርና ማቀነባበሪያና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች የማውረድ ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አክለዉም ክልሎች የችርቻሮ ንግዱንና የአቅርቦት መስመሩን የሚቆጣጠሩ በመሆናቸው፣ በታችኛው መዋቅር ላይ የጥራት ማረጋገጫ ሥርዓት መዘርጋት "የመደራደሪያ ጉዳይ አይደለም" ሲሉ ገልፀዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም የክትትል ሥርዓትን ማጠናከር፣ በሳይንስ ላይ የተመሰረቱ ውሳኔዎችን መውሰድ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን (AI) ጨምሮ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር ማሳደግ እንደሚገባ በመድረኩ ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል።

እንዲሁም በመርሀ-ግብሩ ላይ ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ ገለፃዎችን ያቀረቡ ሲሆንየ2026 (እ.ኤ.አ) የዓለም የምግብ ደህንነት ቀን ዋና መሪ ቃል የሆነውን “ከችግር ወደ መፍትሄ - አስተማማኝ ምግብ በየትኛውም ቦታ” (From Burden to Solutions - Safe Food Everywhere) የሚለውን ሀሳብ መሰረት ያደረገ የፓናል ዉይይትም ተካሂዷል።

6 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.