Logo
EBC
የውስጥ አንድነት - የባዕዳንን ሴራ መስበሪያ መሣሪያ
*****************

(የዕለቱ መልዕክት)

የአንድ ሀገር ሕልውና እና የሕዝቦች ሁለንተናዊ ብልጽግና መሠረቱ የማይናወጥ ዘላቂ ሰላም ነው። አባቶቻችን “ሰላም ለቤት፣ ፍቅር ለጎረቤት” የሚሉት በምክንያት ነው፤ ሰላም ልማት የሚፋጠንበት እና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት የሚገነባበት የሕልውናችን መሠረት ነውና።

ሰላም ሲጠፋ ግን የሀገር መረጋጋት ይናጋል፣ የቆሙበት ምድርም ይንሸራተታል። ባለፉት ዘመናት የታሪክ ትርክቶቻችን ወጥ የሆነ ሀገራዊ መግባባት ከመፍጠር ይልቅ፣ አንዱን ወገን ባለቤት ሌላውን ደግሞ ባዕድ የሚያደርጉ ፅንፈኛ አመለካከቶች መፈልፈያ ሆነው ቆይተዋል። ይህም የጋራ ማንነትን ከመገንባት ይልቅ ቅራኔን እና ቂምን በማስቀደም፣ ለውስጣዊ ግጭቶች መባባስ ማገዶ ሆኖ አገልግሏል።

“አጥር ሲፈርስ አውሬ ይገባል” እንዲሉ በተለይም ጠንካራ እና ገለልተኛ ተቋማት ያልነበሩ መሆኑ፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ወደ ግጭት እንዲያመሩ በማድረግ የሰላም እጦቱን ስር የሰደደ የታሪክ ጠባሳ አድርጎታል።

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መልክዓ-ምድራዊ መገኛ ለሰላሟ መታወክ ሌላኛው ተጠቃሽ ምክንያት ነው። የቀይ ባሕር አቅራቢያ መሆኗ እና የዓባይ ወንዝ መገኛነቷ፣ ታሪካዊ ጠላቶች በውስጥ ጉዳያችን ላይ እጃቸውን እንዲያሰረዝሙ እና ምቀኝነት እንዲያሳድሩ በር ከፍቷል።

እነዚህ የውጭ ኃይሎች በውስጣችን ያሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን በማጉላት ሀገራችን እንድትዳከም ሌት ተቀን ይሠራሉ። “ባንዳ ካልረዳ፣ የውጭ ጠላት አይጎዳ” እንደሚባለው ሁሉ፣ ይህ የባዕዳን ሴራ የሚፈጸመው ደግሞ የሀገርን ሕልውና ለግል እና ለቡድን ጥቅም ሲሉ አሳልፈው በሚሰጡ የሀገር ውስጥ ሆድ አደሮች አማካኝነት ነው።

እነዚህ ኃይሎች የታሪካዊ ጠላቶቻችንን እኩይ አጀንዳ ወደ ውስጥ በማስረግ እና ሕዝባዊ መከፋፈልን በመፍጠር፣ ሀገራችን በራሷ ዜጎች እንድትዳከም ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ አሁንም ከዚህ የክህደት ተግባራቸው አልተቆጠቡም።

ይህንን የጥፋት እና የታሪክ አዙሪት ለመስበር እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ የሚደረግ የፖለቲካ ውድድርን ለማስፈን የለውጡ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ረጅም ርቀት ተጉዟል። ሀገርን ወደ ብልፅግና ለማሻገር የጸና ሰላም እና የቀና ሥርዓት ወሳኞች ናቸው። ስለሆነም ለሰላም ያለው ዕሳቤ ከመደበኛው “ጦርነት አለመኖር” ትርጓሜ የሰፋ እና ጥልቅ መሆን አለበት።

ይህ ዕሳቤ ሦስት ቁልፍ ምሰሶዎችን ያቀፈ ነው፤ አንደኛው ለግጭት መንሥኤ የሆኑ መዋቅራዊ ችግሮች ማለትም ድህነት፣ ኢ-ፍትሐዊነት እና መገለል የተቀረፉበት አዎንታዊ ሰላም መገንባት ሲሆን ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሰላም ከጎረቤቶቿ ሰላም ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን በማመን ለቀጣናዊ ሰላም መከበር የመሪነት ሚና መጫወት ነው። ሦስተኛው እና ዋነኛው ደግሞ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን መፍትሔ በሚለው መርሕ መሠረት፣ ማንኛውንም ውስጣዊም ሆነ አህጉራዊ ግጭቶች በራሳችን ባህላዊ እና ዘመናዊ የሰላም እሴቶች፣ በሽምግልና እና በእርቅ መፍታት ነው።

ኢትዮጵያ ያለችበት ቀጣና ማዕበል የበዛበት እና ውስብስብ ቢሆንም፣ ሀገራችን ግን የሰላም ደሴት ሆና ሰላሟን በማጽናት ሁለንተናዊ ዕድገቷን እያሳለጠች እና የልማት ስበት ማዕከልነቷን እያጠናከረች ትገኛለች።

“ሰላምን ማስፈን ከራስ ይጀምራል” በሚል መርሕ በቀድሞው ሥርዓት በአሸባሪነት የተፈረጁ እና በሐሳብ ልዩነት ተሰስደው የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ታሪካዊ ጥሪ ተደርጎላቸዋል፤ በአሁኑ ወቅትም በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ከዚህም በላይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በፈጠርነው የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ (የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመሠረተ ልማት እና የንግድ) ትሥሥር ምክንያት የእጅ አዙር ጥቃት ሥጋቶች፣ ሽብርተኝነት እና ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲገቱ ተደርጓል።

የመከላከያ እና የደኅንነት ተቋሞቻችንም ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዱ፣ የሀገርን ዳር ድንበር ብቻ የሚጠብቁ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቁ ሆነው በታማኝነት ተገንብተዋል።

በአጠቃላይ አስተማማኝ ሰላምን ማረጋገጥ የሚቻለው የአሸናፊ እና ተሸናፊነትን፣ የቂም እና የቁርሾን ፖለቲካ ማክሰም ሲቻል ነው።

ታሪካዊ ቁስሎችን የምናክመውም በዕርቅ እና በሰላም መንገድ እንጂ በበቀል አይደለም፤ በቀል ማዕበልን እንጂ መረጋጋትን አይወልድምና።

ወደፊትም ሰላምን የሚያደፈርሱ ኃይላትን በሕግ ማስከበር መግታት ብቻ ሳይሆን ለግጭት ምክንያት የሆኑ አለመግባባቶችን በውይይት እና በንግግር ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎችን ዳር ማድረስ ያስፈልጋል።

እንደ ሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግናችንን የሚያፀና ገዥ ትርክት ግንባታችንን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። ሰላምን፣ ትብብርን እና አብሮነትን ብቸኛ አማራጭ በማድረግ የምንከተለው የሰላም መንገድ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም የሚያሻግር፣ ለልጆቻችን የምትመች እና የተከበረች ሀገር የምናስረክብበት ብቸኛው እና አስተማማኙ ጎዳና ነው።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል
#ebc #ethiopia #ebcdotstream #peace #narrative

17 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.