Logo
FIDEL POST NEWS
#update

" አሁንም ምዕመናን ተገድለዋል። እስካሁን 21 ምዕመናንን ቀብረን ተመልሰናል። ተመልሰው እዚያው ቀበሌ ገብተዋል፤ እየገደሉ ነው" - ወረዳ ቤተክህነት

➡️ " 21 መገደላቸውን ትክክለኛ መረጃ ደርሶናል። 8 የደረሱበት አልታወቀም። 8 ሆስፒታል ገብተዋል። ሁለት ታግተዋል "  - የአርሲ ዞን ሀገረ ስብከት

⚫️ " የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ተጨማሪ የሰው ነፍስ እንዳይጠፋ የመከላከሉ ስራ ሊሰራ ይገባል " - ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ

ተደጋጋሚ ግድያ በሚፈጸምበት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ በተፈጸመ አዲስ ጥቃት እስካሁን ባለው መረጃ ብቻ "21 ምዕመናን" በታጠቁ አካላት መገደላቸውን የወረዳው ቤተ ክህነት፣ የዞኑ ሀገረ ስብከት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አርሲ ዞን ሀገረ ስብከት የሽርካ ወረዳ ቤተክህነት አካል በሰጡን ቃል፣ "አሁንም ምዕመናን ተገድለዋል። እስካሁን 21 ምዕመናንን ቀብረን ተመልሰናል" ብለዋል።

ዛሬ ከሰዓት 12 ሰዓት ገደማ ይህን ያሉን እኚሁ የቤተ ክህነቱ አካል፣ የታጠቁት አካላት። "አሁንም ግድያ በፈጸሙበት ቀበሌ ገብተው እያቃጠሉ ነው። ያለው ሁኔታ በዚህ ላይ ነው ያለው" ሲሉም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

አዱሱ ግድያ የተፈጸመው ትናንት (ሐሙስ የካቲት 19 ቀን 2018 ዓ/ም) ጀምሮ መሆኑን ገልጸው፣ የታጠቁት አካላትን "አሁን እኔ እና አንተ በምናወራበት ሰዓት ለማጥቃት ተመልሰው እዚያው ቀበሌ ገብተዋል፤ እየገደሉ ነው" ነው ያሉት።

አመራሩ አዲሱ ግድያ የተፈጸመበት ቀበሌ በሽርካ ወረዳ ጃዌ ዋጩ እንደሚባል የገለጹ ሲሆን፣ አካባቢው አሁንም ከፍተኛ የስጋት ቀጠና ላይ በመሆኑ "ሰሚ ካለ" ትኩረት እንዲሰጥም የሚያሳስቡ መረጂዎችም ከስፍራው እየወጡ ናቸው።

ስለግድያው መረጃ ደርሶት እንደሆነ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ምላሽ የጠየቀው፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የአርሲ ዞን ሀገረ ስብከት በበኩሉ፣ ግድያው እንደአዲስ ተቀስቅሶ ከትናንት ጀምሮ እየተፈጸመ መሆኑን ከወረዳው ቤተክህነት ባገኘው መረጃ መረዳቱን ገልጿል።

አንድ የዞን ሀገረ ስብከቱ አመራር በሰጡን ቃል፣ "የተገደሉት 22 ናቸው እየተባለ ነው። 21 መገደላቸውን ግን ትክክለኛ መረጃ ደርሶናል" ሲሉም ተናግረዋል።

በደረሳቸው መረጃ መሰረት፣ "ሽርካ ወረዳ ጃዊ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የካቲት 19 ቀን ለ20 አጥቢያ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ አንድ ካህን፣ ሁለት ሴቶች እና 18 ወንዶች በድምሩ 21 የንጹሐን ወገኖቻችን ህይወት አልፏል" ብለዋል።

እንዲሁም፣ "ሁለት ሰዎች በታጣቂዎች ታግተዋል። ሌሎች ስምንት ሰዎች ጠፍተው የደረሱበት አይታወቅም። ሌሎች ስምንት ደግሞ በጋምቤላ ሆስፒታል ህክምና ላይ ይገኛሉ" ሲሉ ገልጸውልናል።

የዞን ሀገረ ስብከቱ የካቲት 17 ቀን 2018 ዓ/ም በመርቲ ወረዳ ፈረቀሳ በተባለ ቦታ አራት ሰዎች ተገድለው፣ ከ10 የሚልቁ አባወራ ቤቶች "ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን" አስታውሷል።

የሶማሌ እና ምሥራቅ አርሲ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በበኩላቸው፣  በሽርካ ወረዳ ትናንት 21 ኦርቶዶክሳውያን መገደላቸውን፣ ለማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ገልጸው፣ ከሞቱት 21 ምዕመናን መካከል አንደኛው ካህን እንደሆኑ፣ የሁሉም ስርዓተ ቀብራቸው ዛሬ መፈጸሙን ተናግረዋል።

ሁለት ምእመናን መታፈናቸውን እና ስምንቱ የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ በመግለጽ፣ የአርሲ ዞን ሀገረ ስብከትን ሀሳብ ተጋርተው፣ "ልጆቻችን ሞት የእኛም ሞት ነው" በማለት ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።

"በከንቱ ስለምን ይገድሉናል? የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ተጨማሪ የሰው ነፍስ እንዳይጠፋ የመከላከሉ ስራ ሊሰራ ይገባል" ሲሉም አሳስበዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#tikvahethiopiafamilyaa

tikvahethiopia
5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.