Logo
Getu Temesgen
ለፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ አዳራሽ ተሰየመላቸዉ
#ethiopia | ታላቁ እና አንጋፋው የፊልም ባለሙያ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ “ታሪኩን የማያከብር ትውልድ መቼም ታሪክ አይሠራም፤ እንደ ዓመድ ክምር በኖ እና ተበትኖ ይጠፋል እንጅ።” ይላሉ ኢትዮጵያዊ ፊልም ሠሪ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ።

በዓለም አቀፍ የፊልም ኢንደስትሪው ላይ ጥልቅ እና ዘላቂ ተጽእኖ ፈጣሪው የተወለዱት በጎንደር ከተማ በ1938 ዓ/ም ሲሆን፤ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞው ልዕልት ተናኘ ወርቅ የአሁኑ ኅብረት ት/ቤት እንደተማሩ፤ እውቁ ደራሲው እና አርበኛው አባታቸው ገሪማ ታፈረ እንዲሁም እናታቸው መምህርት ሶፍያ አሁን ለደረሱበት ደረጃ የሕይወታቸውን ጉዞ ተፅዕኖ አሳራፊ እንደነበሩና መንገድ በመክፈት እንዳመላከቷቸው ይናገራሉ።

በ1959 ዓ/ም ኃይሌ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በፈጠራ ጥበብ ማዕከል ውስጥ አጭር ቆይታ ካደረገ በኋላ ድራማ ለማጥናት በልጅነቱ ለፊልም ተዋናይነት እና ደራሲነትን ለመማር ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሰሜን አሜሪካ በማቅናት አንደኛ እና ሁለተኛ ዲግሪውን ያጠናቀቀው።

በዚያን በተማሪነት ዘመኑም ነበር ኃይሌ ሁለት ፊልሞች "Hour Glass" በ1963 ዓ/ም እና "Child of Resistance" በ1964 ዓ/ም የደረሰው። በመጨረሻም መመረቂያ ፊልሙን ስለ እንዲት ጥቁር አሜሪካዊት ዶረቲ የተሰኘች የአንዲት ሴት ልጅ እናት እና ነፍሰ ጡር በድህነት አረንቋ ውስጥ ስለምትኖር ባለቤቷ የቬትናም ዘማች አርበኛ በሐሰት በግፍ በመታሰሯ ይደርስባት የነበረውን ዘረኝነት፣ የፓሊስ ክትትል እና ማሸማቀቅ እንዲሁም ከመንግስት የምታገኘውን ግልጋሎት ቢሮክራሲው ተብትቦ በመያዝ ስለማድረጉ፣ ከፍተኛ ፓለቲካዊ የጥቁሮችን የከተማ የነፃነት ትግል ፍንትው እድርጎ የሚቀሰቅስ እና የሚያታግል "Bush mama" የተሰኘውን ፊልም ለትምህርት መመረቂያ በመድረስ ነበር ትምህርቱን ያጠናቀቀው። የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ ያስታውቃል እንዲሉ አበው እና እመው!

በዚያን ጊዜ ነበር ኃይሌ የፊልም ዳይሬክተር ብቻም ሳይሆን፤ ታሪክ ተራኪ፣ የፊልም ሥራው ለሰው ልጅ ክብር እና መብት ለሚደረግ ትግል በተለይም ለአፍሪካ ብሎም በዓለም ላይ ተበትኖ ለሚኖረው ጥቁር ሕዝብ ፋና ወጊ እንደሚሆን የታመነብነት።

በፊልም በተመረቀ ዋዜማም ነበር ወደ እናት ሐገሩ ኢትዮጵያ በለውጡ ማግስት በ1967 ዓ/ም በመመለስ "የ3000 ዓመት ምርት" የተሰኘውን ጥቁርና ነጭ 16 ሚሊ ሜትር ፊልም የቀረፀው።

ዛሬ ዛሬ በዋሽግተን ዲሲ በሚገኘው ሀዋርድ ዪኒቨርስቲ (Howard University)፣ በካሊፎርኒያ ዩሲ ኤልኤ (University of Los Angles)፣ ኒዎርክ የሚገኘው (The Center for Human Rights and the Arts (CHRA) at Bard College) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የፊልም ከፍተኛ ተቋማት "የ3000 ዓመት ምርት" ፊልምን የአፍሪካ ታሪክ፣ ማሕበራዊ ፍትህ፣ አፍሪካ ድህረ ግኝ ግዛት እንዲሁም ገለልተኛ ፊልም (independent filmmakers) ቀራጮች ሥራ በማለት ለማስተማሪያ ይጠቀሙበታል።

ከ1975 ዓ/ም ጀምሮ በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ በፊልም ፕሮፌሰርነት ለረጅም አመታት በማስተማር ብዙ ጥቁር የፊልም ደረሲያንን ኮትኩቶ በማሳደግ እና በገለልተኛ ፊልም ሥራዎች አንቱ በመባል በጥቁሮች የሲኒማ ታሪክ ላይ ከፍተኛ ማማ ላይ በመድረስ ሎሳጅለስ ካሊፎኒያ የሚገኘው "ዘ አካዳሚ ሙዝየም ኦፍ ሞሺን ፒክቸርስ" የቫንቴጅ ሽልማት የመጀመሪያው ተሸላሚ ኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገሪማ 'ቫንቴጅ' የተባለውን ሽልማት የተሸለሙበትን ምክንያት አስመልክቶ ሙዝየሙ እንዳስታወቀው "በሲኒማ ዙሪያ ዋነኛ ትርክቶችን በመገዳደርና አውድ በማስያዝ የረዳ አርቲስትና ምሁር" በሚል እንዳከበራቸው አስታውቋል። (https://www.nytimes.com/20...

ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ በሠራቸው እና በህዝባዊ ህይወታቻው ሁሉ፤ ኢትዮጵያ ከልባቸው እና ከአፋቸው አትጠፋም። የፊልም ሥራዎቻቸውም በኢትዮጵያዊ ማንነታቸው ላይ የተመሠረተ ቢሆንም ከምንም እና ማንም በላይ በሰፊው የፓን አፍሪካን ራዕይ ግን አስረግጠው ያስተጋባሉ። የፊልም ሚዲያንም ለነጻነት መታገያ፣ ፍትህ ለተጓደለባቸው መሳሪያነት የሚጠቅም ታዋቂ አፍሪካዊ ምሁር እና የሲኒማ ተራኪም በመሆኑ በሰፊው ይከበራሉ።

የፕሮፌሰር ኃይሌ ሥራዎችም በተደጋጋሚ በምዕራባዊያን የፊልም ኢንዱስትሪ አጋፋሪዎች የተገለሉበትን ምክንያትም፤ በድፍረት እውነትን እያቀረቡ ፍትሕና የሰብአዊ እኩልነት ስለሚሰብኩ፣ የዓለም አቀፍ ድምጽ በመሆናቸው እንዲሁም የታሪክ እውነቶችን ለመራቅ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ብዙዎች ይስማማሉ።

ከታዋቂ የፊልም ሥራዎቻቸው መካከል በጥቂቱ በቀዳሚነት የሚታወቁባቸው፦
• አድዋ — የአፍሪካ ድል ( Adwa: An African Victory) አስደናቂ ታሪካዊ ዶክመንተሪ።

• ሳንኮፋ — ስለ ዝርያዊ ባርነት፣ የአፍሪካ ማንናት እና የባህላዊ ነፃነት፣

• ጤዛ — ስለ ስደትና የፖለቲካ ትግል

እነዚህ ፊልሞች የመዝናኛ ብቻ አይደሉም፤ የአፍሪካ ጽናትና በባህል ክብር የተገነቡ እሴቶች ናቸው።

ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ለአበረከቷቸው አስደናቂ የሲኒማ ሥራዎቻቸው ሆነ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን በመስበክ አቻ የማይገኝላቸው ሲሆኑ፤ አፍሪካዊነትንም ከፍ አድርገው የሚያቀነቅኑ ምርጥ አፍሪካዊ ምሁርም ጭምር ናቸው፡፡

ሥራዎቻቸም በአብዛኛው የተጨቆኑ እና የተገለሉ ህዝቦችን ህይወትን ያማከሉ፤ ተቃውሞን፣ ነፃነትንና ፍትህን የሚያበረታቱ ናቸው። ሥርዓታዊ ዘረኝነትን በማጋለጥ እና በእኩልነት ላይ ያለማመንታት ጥብቅና በመቆም ታዋቂ አለም አቀፍ ድምጽ ሆነዋል:: በጥቁር ሕዝቦች ላይ የተፈጸሙ ግፎችን፥ ጭቆናንና ዘረኝነትን ሳይታክቱ ያወገዙና ለእኩልነት የሚታገሉ ዓለምአቀፋዊ የጥበብ ሰው ናቸው።

ይህና ሌሎች በርካታ አበረከቷቸውን ለመዘከርና ትውልድ እንዲማርባቸው ለማድረግ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ሐምሌ 24 ቀን 2017ዓ/ም በማራኪ ግቢ የሚገኘውን የፊልም ትምህርት ክፍል አዳራሽ "ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ሲኒማ አዳራሽ- Prof Haile Gerima Pan-African Cinema Hall" ብሎ በመሰየም ከፍተኛውን የክብር ምልክት ሰጥቷቸዋል።

ዶ/ር አስራት አፀደወይን

10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.