Logo
Getu Temesgen
ከቤት ሰራተኝነት እስከ ባንክ ባለሙያነት
#ethiopia | ገነት ጌታቸው ትባላለች፡፡ ከምድር የነበራት ትውውቅ የጀመረው በውቦቹ መፍለቂያ ወሎ በኩል ነበር፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ተንታ ወረዳ ልዩ ስሙ መቅደላ ወይም ይሎል ተብሎ በሚጠራ ገጠራማ ቦታ ተወለደች፡፡

አስተዳደጓ ከገጠራማ እኩዮቿ ጋር አቻ ነው፡፡ ከብት ስትጠብቅ፣ ውሃ ከምንጭ ስትቀዳና እንጨት ስትለቅም አድጋለች፡፡

በሚገባ መመገብ ከመቻሏ በፊት ምግቧን እያበሰለች ነው ያደገችው፡፡

ለቤተሰቧ ቶና ናት - ፈጣንና ደፋሪቷ ገነት ጌታቸው፡፡ እናቷ በ1983 ከ7ኛ ክፍል ትምህርት አቋርጣ በትዳር ታሰረች፡፡

አባቷ አርሶ አደፋርሶ የሚያበላ ገበሬ ነው፡፡ እናቷ ለትምህርት ልዩ ፍቅር ነበራት፡፡

ትንሿ ገነት የእናቷን የመማር ቁጭት አዝላ አስኳላ ዘለቀች፡፡ ከአንድ እስከ አራት እዛው በቅርቧ ያለ ትምህርት ቤት ተማረች፡፡

ከዚያም በኋላ አምስተኛ ክፍል ለመማር ከምትኖርበት ስምንት ኪሎ ሜትር በየቀኑ እየተመላለሰች ተማረች፡፡

ይህ ስፍራ ተራራማ ቦታ ስለነበር መንገዱ ለትንሿ ገነት ፍጹም አመቺ አልነበረም፡፡ የተሻለ ትምህርት ፍለጋ ዘመድ ጋር መጣች።

የዘመድ ቤት ሌላ ፈተና ሌላ መንገድ ታቅፎ ተቀበላት፡፡ ረሀብ፣ መገረፍ የስነልቦና ጉዳት እና ፍቅር ማጣት እንደ ልጅ አለመታየት የሠርክ ቀለቦቿ ሆኑ።

ብዙ የልጅነት አእምሮዋ መቋቋም የማይችላቸውን አጥንት ድረስ የሚሰረስሩ ንግግሮች ታደምጥ ነበር።

ለትንሽ ልቧ የሚከብደውን ፈተና በምን እንደቻለችው እሷም አታውቅም፡፡ “ምን እንዳስቻለኝ ባላውቅም ሁሉንም እናቴ ለተነጠቀችው ትምህርት ስል ዋጥ አድርጌ አልፈው ነበር” ትላለች።

የቅርብ ዘመዷ (የአጎቷ ልጅ) እሷ እህቴ የምትላት በአንፃራዊነት ጥሩ ነበረች። ብዙ ጫና ታሳድርባት የነበረው የምታኖራት ሴት ነበረች።

ትንሽ ልቧ ብዙ ጊዜ ከቤት ለመጥፋት ከጅሎ ያውቃል። የሶኬት ግርፋት ሰልችቷት ነበር ከቤት ለመውጣት ያሰበችው፡፡

ጠግባ ስለማትበላ ጎረቤት ስትላክ እንጀራ ስጡኝ ማለት ከጅላም ታውቃለች፡፡ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ስምንተኛ ክፍልን ተፈትና ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ተመለሰች፡፡

በዚሁ ቦታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ከመኖሪያዋ 17 ኪሎ ሜትር በየቀኑ መመላለስ ስለከበዳት እዛው ተከራይታ መማር ጀመረች። የ11 እና 12ኛ ክፍል ትምህርቷንም ተጨማሪ 7 ኪሎ ሜትር ተጉዛ ተማረች፡፡

ያኔ ራሷን በገንዘብ መደገፍ ነበረባት፡፡ ለዚያም የተንታ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ውስጥ በተወዛዋዥነት ተቀጥራለች፡፡

የዩኒቨርሲቲ ውጤት እስኪመጣ ድረስ ክረምቱን ከዓመታት በፊት ወደኖረችባት አዲስ አበባ መጣች፡፡ በዚህ ጊዜ የዘመድ ቤት አይታሰብም፡፡

ያንን በመተው በሰው ቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ መስራት ያዘች፡፡ጊዜውን ጠብቆ የዩኒቨርሲቲ ውጤት መጣላት።

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት ዘርፍ ትምህርቷን አጠናች። በዩኒቨርሲቲውም ብዙ ነገሮች አስቻጋሪ ነበሩ፡፡

ክረምት ክረምት አሁንም ያገኘችውን ከመስራት አታርፍም፡፡ በዚህም ጊዜ ሆቴሎች ላይ መስተንግዶ ትሰራ ነበር።

ከሶስት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታ በኋላ ህይወት ሀዋሳ ወሰደቻት። በሀዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክ ከአንድ ዓመት በላይ በረዳት የሰው ኃይል አስተዳደር የስራ መደብ ሰራች፡፡

ቀጥላም ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገባች፡፡ በዚህ ጊዜ ደስታዋ ወደር አልነበረውም፡፡

ቀጥላም ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ ገባች። ቡና ባንክም የተገልጋይ መስኮት የስራ መደብ ከአንድ ዓመት በላይ ሰርታለች፡፡

አሁን ደግሞ በአማራ ባንክ በቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ኦፕሬሽን የስራ መደብ ስር እየሰራች ትገኛለች፡፡

በፕሮጀክት ማኔጅመንት የጀመረችውን የማስተርስ ትምህርት ትምህርትም አጠናቃለች፡፡

አዲስ አበባ የከፈለችው ዋጋ ልጅነቴን ሰርቶታል ትላለች። ጥንካሬዋ የተሰራው እዛ ነው።

ያበረታት የእናቷ ትምህርት አቋርጦ ማግባት ሁልጊዜም ስትቆጭ ስለምታያት በእሷ እንድትካስ ትፈልግ ነበር።

እሱን ለማድረግ መጠንከር የማይሞከረውን መሞከር ነበረባትና በርትታ አሳይታለች።

በዳግማዊት ግርማ
Gazette Plus ጋዜጣ ፕላስ

11 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.