Logo
Getu Temesgen
ወንጌላዊ ኦኔስሞስ ነሲብና ዳግማዊ ምኒልክ፣

(ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በእንግሊዝኛ እንደጻፉት፣ ሲሣይ ተፈራ መኮንን ወደ አማርኛ እንደተረጎመው)
#ethiopia | እንደ ልጅ ልጃቸው አቶ ኢዶሳ ገመቺስ ከሆነ ኦኔስሞስ ነሲብ የተወለዱት በኢሉባቦር ሁርሙ በሚባለው አካባቢ ሲሆን ዘመኑም 1842 ዓ.ም ነው፡፡ የኦኔስሞስ ነሲብ የልጅነት ስማቸው ሂቃ ሲሆን ሂቃ ማለትም በኦሮምኛ ፈቺው ወይም ተርጓሚው እንደማለት ነው፡፡ ወላጆቻቸው እንደትንቢት ሂቃ ብለው የሰየሟቸው ኦኔስመስ፣ ልክ እንደስማቸው የመጀመሪያውን የመጽሀፍ ቅዱስ የኦሮሚኛ ትርጉም በማዘጋጀታቸው ታረክ ሲያስታውሳቸው ይኖራል፡፡

የሂቃ የልጅነት ጊዜ አሳዛኝ ነበር፡፡ አባታቸው በ4 አመት እድሜያቸው እንደሞቱ ሂቃ በባሪያ ፈንጋዮች ታፍነው ተወሰዱ፡፡ ጠረፍ እስከሚደርሱ ድረስም በተለያዩ ጌቶች ስር በባርነት አድረዋል፡፡ አንዳንዶች ሂቃ ነጻ ከመውጣታቸው በፊት 4 ጊዜ በባርነት እንደተሸጡ ሲጽፉ ሌሎች ደግሞ የተሸጡበትን ጊዜ 8 ያደርሱታል፡፡ በመጨረሻም ምጽዋ ላይ በነበረው የፈረንሳይ ቆንሲል ዌርነር ሙዚንገር አማካኝነት ሂቃ ከባርነት ነጻ ወጥተዋል፡፡

ዌርነር ሙዚንገር በጥቅምት ወር 1863 ዓ.ም ከባርነት ነጻ የወጡትን ሂቃ ለስዊድናውያን ሚሲዮኖች ያስረከቡ ሲሆን የሂቃም ህይወት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በዘላቂነት መለወጥ ጀመረ፡፡ በመጋቢት ወር 1864 ዓ.ም የፋሲካ ቀን ዋና ጠባቂ ሆነው በተመደቡላቸው ሉንድሃል አማካኝነት ሂቃ ኦኔስሞስ በሚል አዲስ ስም እንዲጠመቁ ተደረገ፡፡

ኦኔስሞስ ነሲብ በ1868 ዓ.ም ወደ ስዊድን የተላኩ ሲሆን በዛም ለ5 አመት ያህል ሃይማኖታዊ ትምርት ተከታትለዋል፡፡ ከስዊድን እንደተመለሱም የአጼ ቴዎድሮስ የቀድሞ ጸሀፊና የስዊድን ሚሽን ት/ቤት መምህር የነበሩትን የጎጃሙን አለቃ ኃይሉ ልጅ ምህረት ሐይሉን አገቡ፡፡ ከዚህ በኋላም ከንቲባ ገብሩ አቅደው ከፍጻሜ ያላደረሱትን መጽሀፍ ቅዱስን ለኦሮሞ ህዝብ የማስተማር እቅድ በትውልድ አካባቢያቸው ለመፈጸም ሂቃ ወደዛው ለመጓዝ ወሰኑ፡፡

ነገር ግን አጼ ዮሀንስ የሚሲዮናውያንን እንቅስቃሴ አግደው ስለነበር፣ ኦኔስሞስ ወደ ወለጋ ለመጓዝ በቅድሚያ በቀይ ባህር ቀዝፈው ሱአኪን ወደምትባለው የሱዳን ወደብ መጓዝ ነበረባቸው፡፡ ከሱዳን ግዛት ወደ በርበር ካቋረጡ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ጠረፍ ወደ ሚያደርሰው አባይ በመጓዝ በታህሳስ ወር 1875 ዓ.ም ፋማካ ተብላ ወደምትጠራው የጠረፍ ከተማ ደረሱ፡፡ ነገር ግን ወደ ኢትዮጵያ ጠረፍ ማቋረጥ ከጀመሩ በኋላ ችግር እንዳለ በመስማታቸው ለመመለስ ተገደዱ፡፡

የመጀመሪያው ሙከራ ከከሸፈ ከ3 አመት በኋላ በ1878 ዓ.ም ኦኔስሞስ በታጁራና ሸዋ አድርገው ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ለመጓዝ ያደረጉት ጥረትም ንጉሥ ምኒልክ አስቀድመው የሰጡትን ተስፋ በሚጻረር መልኩ የሸዋ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ማቴዎስ ባሰሙት ተቃውሞ ምክንያት ውጤት አልባ ሆነ፡፡ በትውልድ አካባቢያቸው በአካል በመገኘት የወንጌልን ት/ት ለማስፋፋት በተደጋጋሚ ያደረጉት ጥረት ባለመሳካቱ ያዘኑት ኦኔስሞስ ነሲብ መጽሀፍ ቅዱስን የትውልድ አካባቢያቸው ህዝብ በሚገባው የኦሮምኛ ቋንቋ ለመተርጎም ወሰኑ፡፡

የ4 አመት ህጻን ሆኖ የትውልድ አካባቢውን ለለቀቀ ሰው መጽሀፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ መተርጎም ቀላል ባይሆንም፣ ኦኔስሞስ አስቴር ጋኖ በተባሉ የሊሙ ኦሮሞ ወዳጃቸው እየታገዙ የትርጉም ስራቸውን ቀጠሉ፡፡ በመጨረሻም ኦኔስሞስ አዲስ ኪዳንን እና ብሉይ ኪዳንን በቅደም ተከተል በ1885 ዓ.ም እና በ1891 ዓ.ም ወደ ኦሮምኛ በመተርጎም የትርጉም ስራቸውን አጠናቀቁ፡፡ የትርጉም ስራቸውን ለማከናወን በዋነኛነት የተጠቀሙት የአማርኛውን መጽሀፍ ቅዱስ ሲሆን በስዊድን ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሀፍ ቅዱስ ደግሞ ለማመሳከሪያነት ተጠቅመዋል፡፡

የመጀመሪያ ሚስታቸው ወ/ሮ ምህረት ከሞቱ ጥቂት አመታት በኋላ ኦኔስሞስ ሊዲያ ዲምቦ የተባሉትን የወለጋ ሲዮ አካባቢ ተወላጅ አገቡ፡፡ በአስመራ ከተማ ይገኙ ለነበሩ ወደ 500 የሚጠጉ የኦሮሞ ኮሚኒቲ አባላትም የወንጌል ትምህርትን ማስተማር ጀመሩ፡፡ ይህም የትውልድ አካባቢያቸውን ህዝብ በአካል በማስተማር ውጤታማ ስራ ከመስራታቸው በፊት በመፈጸሙ በጎ መንደርደሪያ ሆነላቸው፡፡

በ1885 ዓ.ም ኦኔስሞስ ሚስታቸውን፣ 3 ልጆቻቸውንና አዲስ ሰራተኞቻቸውን በመያዝ ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ተጓዙ፡፡ በአዲስ አበባም በከንቲባ ገብሩ አማካኝነት ኦኔስሞስ ከዳግማዊ ምኒልክና ከአቡነ ማታዎስ ጋር ተገናኙ፡፡ ኦኔስሞስም ለዳግማዊ ምኒልክ የተረጎሙትን የኦሮምኛ መጽሀፍ ቅዱስ ኮፒ በስጦታ አበረከቱ፡፡ በመጨረሻም ኦኔስሞስ በሚጓዙበት ሁሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የሚያዘውን የዳግማዊ ምኒልክ ደብዳቤ ታጥቀው ወደ ወለጋ ተጓዙ፡፡

በወለጋ እንደደረሱም በደጃዝማች ገብረ እግዚአብሔር ሞሮዳ/ኩምሳ ሞሮዳ ከፍተኛ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ ኦኔስሞስ ለመጓዝ ያሰቡት ወደ ትውልድ አካባቢቸው ኢሉባቦር የነበረ ቢሆንም በዳ/ምኒልክና በደጃ/ኩምሳ ሞረዳ በተደረላቸው የክብር አቀባበል ምክንያት ወንጌላዊ ስራቸውን በወለጋ ጀመሩ፡፡ ነጆ አካባቢ በምትገኘው ቦጂ ለኦኔስሞስ መሬት የተሰጣቸው ሲሆን በዛም የማስተማር ስራቸውን ጀመሩ፡፡

የኦኔስሞስን ሃይማኖታዊ ትምህርት በአደጋነት የተመለከቱ የኦርቶዶክስ አባቶች ባቀረቡት ክስ ምክንያት ኦኔስሞስ ወደ አዲስ አበባ ከተጠሩ በኋላ በአቡነ ማቴዎስ የእስራት ፍርድ ተፈረደባቸው፡፡ ነገር ግን ዳግማዊ ምኒልክ የአቡኑን ፍርድ ባለመቀበል ጉዳዩ በድጋሚ በአፈ ንጉሥ ኢስጢፋኖስ እንዲመረመር አዘዙ፡፡ በዚሁ መሰረት አፈ ንጉሡ ጉዳዩን በድጋሚ መርምረው ኦኔስሞስን ከቀረበባቸው ክስ በነጻ አሰናበቱ፡፡

ዳግማዊ ምኒልክ ከዚህም አልፈው ለኦኔስሞስ በንግድ ሚኒስቴር ስራ እንዲሰጣቸው አዘው የነበረ ቢሆንም፣ በወቅቱ የነበሩት ሹማምንት ኦኔስሞስ በንግድ ጉዳይ ለመስራት የሚያስችል እውቀትና ክህሎት የላቸውም በሚል የምኒልክን ትዕዛዝ ሳይፈጽሙ ቀርተዋል፡፡ ኦኔስሞስ ነሲብ ወደ ወለጋ ተመልሰው በተለይም ከልጅ ኢያሱ ዘመን ጀምሮ በነጻነት ሲያስተምሩ ከቆዩ በኋላ በሰኔ ወር 1923 ዓ.ም በድንገት ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ነፍስ ይማር!

ምንጭ፣ Pioneers of Change in Ethiopia: The Reformist Intellectuals of the Early 20th Century, Prof Bahru Zewde, PP.46-49

ምስል፦ ኦኔስሞስ ነሲብ ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋራ ኤርትራ ውስጥ የተነሱት ፎቶግራፍ ነው፡፡ ፎቶው የመቼ እንደሆነ አልተገለጸም። #jemal_abdulaziz

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.