Logo
Getu Temesgen
የቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህንጻ ተመረቀ
#ethiopia | በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ በ120 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህንጻ ግንባታ ተጠናቆ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዋና ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በተገኙበት ተመረቀ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ መንግስት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰፊ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል። ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ የቆንዳን ጨምሮ አራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል። የሆስፒታሉ መገንባት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክር ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፣ ሆስፒታሉ የተሟላ የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ህብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው፣ የቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለክልሉ የጤና ሽፋን ዕድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። የክልሉ መንግስት የጤና ተቋማትን ተደራሽነት ለማረጋገጥ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም፣ የቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በ120 ሚሊየን ብር መገንባቱን ገልጸዋል። ይህ ሆስፒታል በክልሉ 12ኛው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሲሆን፣ የሆስፒታል ሽፋንን ከ32 በመቶ ወደ 33.4 በመቶ ከፍ ማድረጉን አስረድተዋል። ሆስፒታሉ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ የሕክምና ቁሳቁስ ለማሟላት ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የክልሉ መንግስት የዘገዩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ ለማስቻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የቆንዳ ሆስፒታልም ከነባር ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች አንዱ በመሆኑ፣ የክልሉ መንግስት በሰጠው ትኩረት ዛሬ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ብቁ መሆኑን አክለዋል።

የገዋታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አርጋው ኃይሌ በምረቃ መርሐግብሩ ላይ እንደገለጹት ፣ የሆስፒታሉ አስፈላጊነት በሕዝቡ በኩል ከ2008 ዓ.ም ሲቀርብ የነበረ ጥያቄ ነው። አካባቢው ከዞኑ ማዕከል የቦንጋ ከተማ በመራቁ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት ትልቅ ችግር ነበር። የሕዝቡን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የቀድሞ የደቡብ ክልል ይሁንታ ሰጥቶ በ2009ዓ.ም ግንባታው በይፋ ተጀመረ።

ጂኤንድኤስ ቢውልዲንግ ኮንስትራክሽን ( G & S bulding contractor plc ) ፕሮጀክቱን ከተረከበ በኋላ ግንባታውን ያለምንም እንከን ማጠናቀቁን አቶ አርጋው አብራርተዋል። የቁሳቁስ ዋጋ ንረት ሳይገድበው ያለምንም መስተጓጎል ሥራውን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቁ ክብርና ምስጋና ይሰጠዋል ብለዋል።

አቶ አርጋው ኃይሌ ለሆስፒታሉ አገልግሎት አስፈላጊ የሆኑ ትራንስፎርመርና የውሃ ግንኙነት በውል ውስጥ ባይካተቱም፣ የክልሉ መንግሥት ለቀረበለት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው ፣ አሁንም የውስጥ ሕክምና ቁሳቁሶች ግዥ አለመከናወኑን እና እነዚህ ቁሳቁሶች በፍጥነት ተማልተው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ጠይቀዋል።

የገዋታ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱ አባጊዲ፣ የቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለዘጠኝ ዓመታት የሕዝቡ ከፍተኛ ጉጉት የነበረው ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል። ግንባታው በ13 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ለዚህም 11 አርሶ አደሮች ይዞታቸውን በፈቃደኝነት ለቀው መስጠታቸውን አስረድተዋል። ሆስፒታሉ መከፈቱ በአካባቢው ለሚኖሩ እናቶችና ህፃናት በ84 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኙ የሕክምና ተቋማት ይደረግ የነበረውን የሪፌራል አገልግሎት ችግር በመፍታት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖውን እንደሚቀንስ ተናግረዋል።

አቶ አብዱ አያይዘውም የገዋታ ወረዳ ብቻውን 110 ሺህ የሚሆን ሕዝብ ያለበት ሲሆን፣ ከኦሮሚያ ክልል አጎራባች ቀበሌዎች እንዲሁም ከጌሻ፣ ከሳይለም እና ከደካ ወረዳዎች ነዋሪዎች የሆስፒታሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።

የጂኤንድኤስ ኮንስትራክሽን ጠቅላላ የፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ ከላሌ ታደሰ በበኩላቸው፣ የቆንዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የ120 ሚሊየን ብር ፕሮጀክት እንደነበር እና የዘጠኝ ወር የጊዜ ገደብ ተሰጥቶት በጥራት እና በሰዓቱ ለማስረከብ መቻሉን ገልጸዋል። ጂኤንዲኤስ ኮንስትራክሽን ከአስር ዓመት በላይ የሥራ ልምድ እንዳለው እና በመንገድ፣ በህንፃ፣ በውሃ እና በሪል እስቴት ግንባታ ዘርፎች እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የጂኤንዲኤስ ቢውልዲንግ ኮንስትራክሽን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ገበረኪሮስ አማረ በበኩላቸው፣ ኩባንያቸው በፕሮጀክቱ ሂደት ውስጥ ያጋጠሙትን የተለያዩ ፈተናዎች በተለይም የቁሳቁስ ዋጋ መናርን ተቋቁሞ፣ የታቀደውን የጊዜ ገደብ በማክበርና በጥራት ሥራውን ማጠናቀቁን ገልጸዋል። ይህ ፕሮጀክት በኩባንያቸው የረጅም ጊዜ የሥራ ልምድ እና ብቃት ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ለክልሉ ልማት አስተዋፅኦ በማድረጋቸው መደሰታቸውን አሳይተዋል።

የምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የካፋ ዞን አመራሮች፣ የቆንዳ ከተማ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.