Logo
EBC
የመስከረም ብርሃን እና የሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችን አዲስ ምዕራፍ ለአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ እና ሀገራዊ መግባባት
***************************

የመስከረም ወር ሲጠባ የሚፈነጥቀው የብርሃንና የተስፋ ጭላንጭል ለኢትዮጵያውያን የዘመን መለወጫ በዓል ብቻ ሳይሆን፣ ያለፈውን አሮጌ ታሪክ አልፎ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትንና ሀገራዊ መግባባትን የምናጠናክርበት አዲስ ምዕራፍ ነው።

አዲስ ዓመት አዳዲስ ሀሳቦች የሚመነጩበትና ለነገዋ ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ የሚሰነቅበት ወቅት በመሆኑ ባሳለፍናቸው ጊዜያት የታዩ መልካም ሀገራዊ ስኬቶችን በማጠናከርና ከገጠሙ ፈተናዎች ደግሞ ተገቢውን ትምህርት በመውሰድ ወደፊት መራመድ ይገባል።

በተጠናቀቀው ዓመት ሀገራችን የሀገራዊ የምክክር ጉባኤን በስኬት መጠናቀቅ ተከትሎ፣ የውይይት ባህልን በማጎልበት በልዩነቶች መካከል የጋራ መግባባትን አበክራ ሰርታለች።

ይህ ስኬት ከኮሪደር ልማት፣ ከገበታ ለሀገር፣ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን ከመትከል መርሃ-ግብር እና ከኢንቨስትመንት እድገት ጋር ተጣጥሞ በመሄዱ ለዘላቂ ልማትና ለነገዋ ኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ጥሏል።

በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚፈጠሩ ውስብስብ ሀገራዊ ችግሮች ቢኖሩም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያዳበረው የሕብረ-ብሔራዊ አብሮነት የመደጋገፍና የመከባበር እሴት ሀገራዊ ህልውናችንን አስከብሮ እንድንሻገር አስችሎናል።

በዚህ ረገድ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአባገዳዎች ሚና የጎላ ነበር። በተለይም በዩኔስኮ የተመዘገቡት የመስቀል ደመራ፣ ኢሬቻ እና መሰል ሕዝባዊ በዓላት የሚከበሩበት ይህ የመስከረም ወር የወንድማማችነትና የትብብር መንፈሳችንን የሚያድስበት ልዩ አጋጣሚ ነው።

ኢትዮጵያውያን በአብሮነት የተጋመድን፣ ለሀገራችን ሉዓላዊነት እኩል ዋጋ የከፈልንና መልካም እድሎችንና መከራዎችን እኩል የተጋራን ነን።

ትናንት በአድዋ ድል ዛሬ ደግሞ በእኛ ትውልድ ዳግማዊ አድዋ በሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብና በሌሎችም አንጸባራቂ ድሎች በአብሮነት ደምቀን መታየት ችለናል።

ሕብረ-ብሔራዊነት በዜጎች መካከል እውነተኛ ወንድማማችነትን የሚያጎለብትና ብሔራዊ መግባባትን የሚያረጋግጥ ዘመኑን የዋጀ ገዢ ትርክታችን ነው።

ይህ ታላቅ ገዢ ትርክት የልዩነት መነሻ የሆኑትን ችግሮች በውይይት በመፍታት አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በይቅርታና በእርቅ በመፍታት በልዩነቶች ውስጥ የመግባባትና የመተባበር ባህልን መገንባትን ዓላማው አድርጓል።

ብዝኃ-ማንነትን በአግባቡ ማስተናገድ የተዛቡ ግንኙነቶችን የሚያርቅና የብዝኃነት ጸጋዎችን የሀገር ሀብት አድርጎ ለመጠቀም የሚያግዝ ነው።

ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት በቅን ልቦና፣ በአዲስ መንፈስና በጋራ ትብብር በመቀበል የሀገራችንን ሰላም፣ አንድነትና ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ማድረግ ይኖርብናል።

በብሌን ደምበሎ
#ethiopiannewyear #nationalunity #ethiopiarising #inclusivity #greenethiopia

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.