Logo
EBC
የነገዋ ኢትዮጵያ አስተማማኝ ምሶሶ፡ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና ያልተነካው የወጣቶች አቅም
*******************************

ኢትዮጵያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በበርካታ ዘርፎች እያሰመዘገበችው ያለው ሁለንተናዊ የልማትና የመዋቅር ለውጥ የሀገራችንን ገጽታ ሙሉ በሙሉ እየቀየረው ይገኛል። ከተሞች ከነበሩበት የቆየ አሰራር ወጥተው ዘመናዊና ለኑሮ ምቹ ሆነው እንዲደራጁ ከተደረገበት የኮሪደር ልማት ጀምሮ፣ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው እመርታ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት እና የፋይናንስ ዘርፉ መከፈት ሀገራችንን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ያሸጋገሩ ታላላቅ ማሳያዎች ናቸው።

ነገር ግን ከእነዚህ ሁለንተናዊ እመርታዎች ሁሉ በላይ የነገዋን ኢትዮጵያ ቅርፅና አቅም የሚወስነው ዋናው አስተማማኝ ምሶሶ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተቀረጸው «ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030» ስትራቴጂ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ እንደገለጹት፥ የቴክኖሎጂ ዘርፉ የአሠራር ማሻሻያ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ብልጽግናችንን የሚያረጋግጥና የዜጎችን ህይወት በዘላቂነት የሚያቃና ዋና የኢኮኖሚ ሞተር ነው። የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ በውጭ እርዳታ ወይም በባህላዊ አሠራሮች ላይ ብቻ መመስረት እንደማይቻል በመገንዘብ ሀገራችን፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ መሪ ኢኮኖሚ የመገንባቱን ሂደት በጥንካሬ ተያይዛዋለች።

ዲጂታል 2030 የመንግሥት አገልግሎቶችን ግልጽና ፈጣን ከማድረግ ባሻገር፣ እንደ «ፋይዳ» ዲጂታል መታወቂያ፣ «መሶብ» የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቋት እና ዲጂታል የክፍያ ስርዓቶችን በመዘርጋት ሀገራችንን ከአካታች የዲጂታል አሠራር ጋር አስተስስሯታል።

ሆኖም ግን ይህ ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ ያለ ወጣቱ ንቁ ተሳትፎ እና ግንባር ቀደም መሪነት እውን ሊሆን አይችልም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ትልቁና ያልተነካ ተፈጥሮአዊ ሀብት ወጣቱ ህብረተሰብ ነው።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ከሚሆነው የሀገራችን ህዝብ አብዛኛው ክፍል ወጣት በመሆኑ፣ ይህን አቅም በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራና በክህሎት ማነጽ ከተቻለ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና አሸናፊ መሆን እንደምትችል ይታመናል።

ወጣቱ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን የችግር ፈቺ መፍትሔዎች አቅራቢና የራሱን ቢዝነስ የሚፈጥር እንዲሆን የተዘረጉት የኢኖቬሽን ስነ-ምህዳሮች የዚሁ አመለካከት ውጤቶች ናቸው።ለዚህም ነው ወጣቱን የዲጂታል አብዮቱ ዋና መሪ ለማድረግ ታሪካዊው የ«5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች» ኢኒሼቲቭ በይፋ የተበሰረው።

ወጣቶች በሶፍትዌር ልማት፣ በዳታ ሳይንስ፣ በአንድሮይድ አፕሊኬሽን እና በአርቲፊሻል ኢንቴሊጀንስ በነጻ ሰልጥነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መንገድ ተከፍቶላቸዋል። ይህ ስልጠና ወጣቶች በሀገራቸው ተቀምጠው የዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን የቴክኖሎጂ ስራዎች በመስራት የውጭ ምንዛሬ እንዲያመጡ፣ የራሳቸውን ስታርት-አፕ ኩባንያዎች እንዲመሰርቱና ለሌሎችም የሥራ እድል እንዲፈጥሩ የሚያስችል ታላቅ የክህሎት ድልድይ ሆኗል።

በሀገራችን በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተመዘገቡት የልማት ስኬቶች መነሻ ተደርገው ሲወሰዱ፣ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የቴክኖሎጂ እቅድ ብቻ ሳይሆን የወጣቱን ዘመናዊ አቅም በመጠቀም የኢትዮጵያን ብሩህ ነገ እውን የሚያደርግ ታላቅ ህዝባዊና ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።

የመንግስት ፖሊሲ፣ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት እና የወጣቱ የፈጠራ አቅም ሲቀናጁ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተገለጸው በ2030 ኢትዮጵያን በአፍሪካ አህጉር በዲጂታል ኢኮኖሚ የጎለበተችና የበለፀገች ተፎካካሪ ሀገር የማድረግ ህልማችን በትብብርና በጋራ እውን ይሆናል።

በሔዋን ጌታቸው
#ethiopia #digitalethiopia2030 #youthintech #5millioncoders #digitaltransformation #innovation #ebc

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.