Logo
EBC
የትግራይን ወጣት ከብርሃን የለየው ትውልድ በላው የክፋት ቋት
****************

ሥልጣን እና የዘረፋ ገንዘብ ለማካበት ሲል የተጠነሰሰው ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን፣ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በትግራይ ወጣቶች ደም መኖርን ብቸኛ የህልውናው ማረጋገጫ አድርጎታል።

ይህ የክፋት ቋት የሆነው አረመኔ ቡድን የትግራይን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መዋቅር አፈራርሶ፣ የደም ነጋዴነቱን ዛሬም ድረስ አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ቡድኑ የትግራይን ወጣት የሰው ኃይል ለጥቂት አመራሮቹ ስግብግብ ፍላጎት እና ወታደራዊ እብደት ማሳኪያ በማድረግ በርካታ እናቶችን ያለ ጧሪና ደጋፊ ያስቀረ ጨካኝ ስብስብ ነው።

ይህ ደም መጣጭ ቡድን በይፋ ባወጣው የግዳጅ አፈሳ አዋጅ፣ ምስኪኑን የትግራይ ወጣት ወደማያባራ የጦርነት እሳት እየማገደው ይገኛል። ያልታፈሱት ደግሞ ከዚህ የክፋት ኃይል አፈና ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ፣ ቀን ከሌት በየገደሉ እና በየጫካው እየተሽሎከሎኩ የፍርሃት ኑሮን ለመግፋት ተገደዋል።

የቡድኑን የጥፋት አዋጅ የተቃወሙ እና ልጆቻቸውን ለሞት አንሰጥም ያሉ ቤተሰቦች በእስራት፣ በድብደባ እና ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀል ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ።

ይህን በደል የጭካኔ ጥግ የሚያብለው ደግሞ፣ የሕገ-ወጡ ቡድን አመራሮች የሚሠሩት አስነዋሪ ድርጊት ነው። እነዚህ የጥፋት ሐዋርያት የገዛ ልጆቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን በአውሮፓ እና በአሜሪካ ታላላቅ ከተሞች በተንደላቀቀ የቅንጦት ሕይወት እያኖሩ እና በውድ ትምህርት ቤቶች እያስተማሩ፤ የድሃውን ልጅ ግን በግዳጅ አፍሰው ለጥይት ማብረጃነት ይገብሩታል። የትግራይ እናት በልጇ መርዶ ደም ዕንባ ስታለቅስ፣ የአመራሩ ልጆች ግን በምዕራቡ ዓለም በዘረፉት የሕዝብ ሀብት ይንደላቀቃሉ።

በዚህ የክረምት ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች የወደፊት ብሩህ ሕይወታቸውን የሚገነቡበት ወርቃማ ዕድል አግኝተዋል። በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በተጀመረው እና ዒላማውን ወደ ሰባት ሚሊዮን ባሳደገው የ"አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች" ታላቅ ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ፣ መላው የሀገሪቱ ወጣቶች በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስ፣ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዘርፎች ነፃ የሥልጠና ዕድል እየተጠቀሙ መጻኢውን ዓለም እየተቀላቀሉ ነው።

ሆኖም በዚህ አጥፊ ቡድን የታገተው የትግራይ ወጣት ከዚህ ወርቃማ የዕረፍት ጊዜ እና ሀገራዊ የቴክኖሎጂ አብዮት ተነጥሎ በሞት ጥላ ሥር እንዲያልፍ ተፈርዶበታል።

ይህ ፀረ-ሕዝብ ቡድን የትግራይን ወጣት ከዲጂታሉ ዓለም እና ከሥልጣኔ አግልሎ፣ ትምህርት ቤቶችን የጦር ካምፕ አድርጎ፣ ዛሬም የሕዝብን ስቃይ ለፖለቲካ ቁማር እና ለልመና ንግድ እየተጠቀመበት ነው።

ልክ በ1977ቱ የድርቅ ጊዜ ለእርዳታ የመጣውን እህል ሸጦ ሕዝብን ለርሃብ እንደዳረገው ሁሉ፣ አሁንም በፈጠረው ቀውስ ኅብረተሰቡን ለዕርዳታ ጥገኛ አድርጎታል። ይህ ደግሞ መጻኢውን የክልሉን ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ወደሆነ አቅጣጫ እየመራው ይገኛል።

ስለሆነም የትግራይ ሕዝብ እና ወጣቱ ይህን የክፋት ምንጭ እና ትውልድ ገዳይ ተባይ ከላዩ ላይ አራግፎ በመጣል፣ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር የሰላም፣ የትምህርት እና የልማት ተጠቃሚ ወደሚሆንበት ብርሃናማ መንገድ ሊወጣ ይገባል።
#ethiopia #tigray #youths #ethiocoders #digitalethiopia #ebc

1 day ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.