Logo
Ethio telecom
ኩባንያችን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ በዜድ.ቲ.ኢ (ZTE) ኮርፖሬሽን ኤክስክዩቲቭ ቫይስ ፕሬዝደንት እና ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር ሚስተር ዢ ጁንሺ ከተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር በባርሴሎና በተካሄደው የሞባይል ወርልድ ኮንግረስ 2026 (MWC2026) ላይ የተፈረሙትን ወሳኝ የኔትወርክ ማስፋፊያና ማዘመኛ ፕሮጀክቶች በስኬት መጠናቀቅ ተከትሎ ስትራቴጂያዊ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ በዜድ.ቲ.ኢ የፕሮጀክት ሰርክል በሚገኙ 879 ጣቢያዎች ላይ የተከናወኑ የኔትወርክ ማስፋፊያና የማዘመን ሥራዎች በስኬት መጠናቀቃቸው ተበስሯል። ይህ ስኬት በዜድ.ቲ.ኢ ሰርክል የሚገኘውን የ4ጂ (4G) ሞባይል ኔትወርክ የሕዝብ ተደራሽነት ሽፋን ወደ 92% ያደረሰ ሲሆን፤ ይህም የሀገራችንን የዲጂታል ኢኮኖሚ በማጠናከር የበርካታ ዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል።

የኩባንያችን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የፕሮጀክቱን ስኬታማ አፈጻጸም በእጅጉ አድንቀው፣ የ«ቀጣዩ አድማስ» ስትራቴጂ የአንደኛ ዓመት ግቦችን ለማሳካት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ዜድ.ቲ.ኢ ፕሮጀክቱን በጥራትና በወቅቱ ለማጠናቀቅ ላሳየው ቁርጠኝነት እንዲሁም ለተገበራቸው የፋይናንሲንግ አማራጮች አድናቆት ሰጥተዋል።

አክለውም ቀጣዩ የኔትወርክ ማዘመኛ እና የማስፋፊያ ምዕራፍ በታላላቅ ግቦች እንደሚቀጥል አጽንኦት የሰጡ ሲሆን፣ የዜድ.ቲ.ኢ ቡድንም ያላሰለሰ ድጋፉን በዘላቂነት እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። ይህ አጋርነት የኔትወርክ ማሻሻያዎች በፍጥነትና በብቃት እንዲተገበሩ በማድረግ፣ የሀገራችንን ጥራት ያለው የዳታ አገልግሎት ፍላጎት ለማርካት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አጽንኦት ሰጥተውበታል።

በቀጣይም ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ስማርት ስልኮችን ተደራሽ የሚያደርጉ የዲቫይስ ፋይናንሲንግ አማራጮችን በጋራ ስለማስጀመር የተወያዩ ሲሆን፤ ይህም ደንበኞች ዘመናዊ የቴሌኮም መሣሪያዎችን በስፋት እንዲጠቀሙ በማስቻል ለአካታች የዲጂታል ማኅበረሰብ ግንባታ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ታምኖበታል።

በተጨማሪም የ"አረንጓዴ ኦፕሬተር" (Green Operator) ኢኒሼቲቭን ማፋጠን ያለመ ውይይት በማድረግ፤ በዘላቂ የአረንጓዴ ኢነርጂ መሠረተ ልማት ላይ በጋራ በመሥራት ከቴሌኮም ኦፕሬሽናል ሥራዎች የሚወጣውን የካርቦን ልቀት በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

በመጨረሻም የዜድ.ቲ.ኢ ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር (COO) የኩባንያችንን አስደናቂ ዕድገትና ስትራቴጂ ያደነቁ ሲሆን፣ ዜድ.ቲ.ኢ ከአፍሪካ ቀዳሚ የቴሌኮም ኦፕሬተር ከሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ጋር በከፍተኛ ደረጃ የመሥራት ዕድል በማግኘቱ የተሰማቸውን ኩራት በመግለጽ፤ አጋርነታቸውን አጠናክሮ ለመቀጠል ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት አረጋግጠዋል።

ተጨማሪ፡ https://bit.ly/3RZXCxm

1 day ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.