Logo
EBC
የጅማ ዞን በበቆሎ ልማት ያስመዘገበው አዲስ የስኬት ምዕራፍ
********************

የጅማ ዞን በአብዛኛው ጥራትና ብዛት ባለው የቡና ምርቱ የሚታወቅ ሲሆን አሁን ላይ በዞኑ በክላስተር የለማው የበቆሎ ሰብል የግብርና ልማት ለሌሎች በምሳሌነት የሚጠቀስ ሆኗል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ፤ ዞኑ ሀገራችን ከቡናው ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝና መልካም ስም እንድትጎናፀፍ ከማድረጉም ባሻገር ዛሬ በተለያዩ የሰብል ምርቶች አዲስ ስኬት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት ፅሁፍ፤ በተለይም በጊቤ ወንዝ ሸለቆ ዳርቻ በሚገኘው በቦቶር ጦላይ ወረዳ በክላስተር የለማው በቆሎ ሰፊ መሬት በመሸፈን የግብርና ክላስተር ልማት አርአያ ሆኖ ይታያል ብለዋል።

በአጠቃላይ በቦቶር ጦላይ ወረዳ በሚገኙ 16 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ 9,540 አርሶ አደሮች በ19,778 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎን በክላስተር ማልማታቸውን የገለጹት አቶ አዲሱ አረጋ፤ በጅማ ዞን ደረጃ 198,115 ሄክታር መሬት በቆሎ በክላስተር የለማ ሲሆን ከሄክታር በአማካይ 80 ኩንታል ምርታማነት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

ይህ ሥራ ምርታማነትን በመጨመር፣ የአርሶ አደሮችን ገቢ በማሳደግና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

5 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.