Logo
EBC
ጽኑ የሕዝብ አንድነት እና ብቁ የጸጥታ ተቋማት፡ የኢትዮጵያ ከፍታ ዋስትና
********************
(የዕለቱ መልዕክት)

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ሥርዓተ መንግሥት ያላት ታላቅ ሀገር በመሆኗ ምንም ዓይነት የጥፋት ኃይል ሰላሟን በቀላሉ ማናጋት እንደማይችል በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ የሚለው ስም ለችግሮች አለመንበርከክ፣ በፈተና ሳይበገሩ የማለፍ እና እንቅፋቶችን ተሻግሮ ድል የማድረግ የክብር ማህተም ነው።

ሀገራችን በታሪኳ ያለፈተና ያሳለፈቻቸው ዘመናት እጅግ ጥቂት ቢሆኑም፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን ታሪካዊ ክብራችንን እያስጠበቅን ነው።

በተለይም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ወደ ኋላ የማይደራደር ጠንካራ መንግሥት መኖሩን የተረዱ በዓባይና በአፍሪካ ቀንድ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጥፋት ናዳቸውን ሲያወርዱ ቆይተዋል።

ሆኖም እነዚህ የክፋት ኃይላት በሀገራችን ላይ የሚረባረቡት መጪውን ብሩህ ዘመናችንን አይተው እንጂ ተስፋ ቢስ ድሆች መሆናችን አስጨንቋቸው አይደለም።

ዓላማ የሌላቸው አጥፊዎች የሚያደርሱትን የውስጥ ፈተና እና የውጭ ጫና ተቋቁመን በድል ላይ ድል የምንቀዳጀውም በሕዝባችን አንድነት እና በጸጥታ ተቋሞቻችን ብቃት ነው።

ይህ የጸጥታ ተቋማት ብቃት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተከናወኑ መጠነ-ሰፊ ሀገራዊ ሪፎርሞች የተገኘ ፍሬ ነው።

ተቋማቱ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የጸዱ፣ ለሕገ-መንግሥቱና ለሕዝብ ብቻ ታማኝ የሆኑ እንዲሁም የሀገራችንን ሉዓላዊነት በጽናት የሚያስጠብቁ ሆነው ተገንብተዋል።

በዚህም መሠረት የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የአየር ኃይል የላቁ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን እና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ስልታዊ ድሮኖችን በመታጠቅ የአየር ክልላችንን ፍጹም የማይደፈር አድርገውታል።

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይልም የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም እና ቀጣናዊ ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ ሌት ተቀን እየተጋ የሚገኝ ተቋም ሆኗል።

የዘመኑ ጦርነት በቴክኖሎጂ የሚመራ በመሆኑ በሳይበር ምህዳር ሀገርን ለመጠበቅ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር እንዲሁም ስትራቴጂያዊ መረጃዎችን አስቀድሞ በመተንተን ሴራዎችን የሚያከሽፈው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ወደር የለሽ አቅም ገንብተዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ አቅሙን በፎረንሲክና በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማዘመን የአሻጥር፣ የሌብነት፣ የኮንትሮባንድ፣ የሙስና እንዲሁም ሕገ-ወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎችን በመከላከል የሕዝቡን ሰላም እያስከበረ ይገኛል።

እነዚህ ተቋማት ጠላቶች የሚነዙትን የሥነ-ልቦና ጦርነት እና ድብቅ ሴራዎች አስቀድመው በማምከን የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንቶች መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል።

የኢትዮጵያ ጂኦ-ፖለቲካዊ ኩስምና ባከተመበትና አቋሟ እየተስተካከለ በመጣበት በዚህ ወቅት የጸጥታ ተቋሞቻችን የሀገራችንን ሉዓላዊነት፣ ዳር ድንበርና የብልጽግና ጉዞ ለማስከበር በሚያስችል አስተማማኝ የወትሮ ዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ይህንኑ ዝግጁነት ይበልጥ በማጠናከር እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማረጋገጥ የውስጥና የውጭ ችግር ፈጣሪዎችን አደብ ማስገዛት የህልውናችን መሠረት ነው።

የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ሀገርና ሕዝብን በማስቀደም በጀግንነት የሚከፍሉት መስዋዕትነት፣ ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥበብ እና ጽናት የምትመራ፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ ፈተናዎችን አልፋ ለትውልድ የምትተርፍ የኩራት ምንጭ መሆኗን ያረጋግጣል።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.