Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ዛሬ የአሜሪካን ባለስልጣናት እንዳረጋገጡት፣ በዩታህ ግዛት የተነሳውን ሰደድ እሳት በማጥፋት ላይ የነበሩ ሁለት የሄሊኮፕተር አብራሪዎች ተከስክሰው ህይወታቸው አልፏል። የሴቪየር ካውንቲ ፖሊስ (ሸሪፍ) እንደገለጸው፣ አብራሪዎቹ ህይወታቸውን ያጡት አርብ ጠዋት 'ሲኮርስኪ ስካይክሬን' የተሰኘው ሄሊኮፕተራቸው በመከስከሱ ነው።

ሄሊኮፕተሩ በ'ፊሽሌክ' ብሔራዊ ደን ውስጥ የተነሳውን እሳት ለማጥፋት ከተሰማሩት ውስጥ አንዱ ነበር። የመከስከሱ አደጋ አዲስ እሳት ያስነሳ ሲሆን፣ ይህም ከነበረው ሰደድ እሳት ጋር በመቀላቀል በአሁኑ ወቅት 451 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ መሬት አውድሟል።

ባለስልጣናቱ የአብራሪዎቹን ማንነት ባይገልጹም፣ በአሜሪካ የደን አገልግሎት ስራውን በተረከበ 'ሄሊኮፕተር ትራንስፖርት ሰርቪስ' በተሰኘ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥረው ይሠሩ እንደነበር አስታውቀዋል። በእሳቱ ግለት ምክንያት የነፍስ አድን ሰራተኞች ወዲያውኑ አደጋው ወደ ደረሰበት ቦታ መድረስ አልቻሉም ነበር። ነገር ግን ቅዳሜ ዕለት የነፍስ አድን ሰራተኞች ወደ ስፍራው በመግባት የሞት አደጋውን ማረጋገጥ መቻላቸውን የሴቪየር ካውንቲ ፖሊስ እና የህክምና መርማሪዎች ገልጸዋል። የብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ የሄሊኮፕተሩን ስብርባሪ መመርመር ሲጀምር ማጣራቱን የሚያካሂድ ሲሆን፣ የአደጋውን ትክክለኛ መንስኤ ለማወቅ አንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ሊወስድ እንደሚችል ተገምቷል።

በተመሳሳይ በምዕራባዊ የአሜሪካ ክፍሎች በርካታ ሰደድ እሳቶች እየተቀጣጠሉ ይገኛሉ። በዋሽንግተን ግዛት በሚገኘው 'ማውንት ሬኒየር' ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በተነሳ አዲስ እሳት ምክንያት፣ የብሔራዊ ፓርክ አገልግሎት ወደ 'ሰንራይዝ' እና 'ዋይት ሪቨር' የሚወስዱ መንገዶችን ለጎብኚዎች ዘግቷል። የእሳት አደጋ ተከላካዮች ይህንን እሳት ለመቆጣጠር ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ። በስፖካን፣ ዋሽንግተን አቅራቢያ የተነሱት ትላልቅ እሳቶች ደግሞ ከ40 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ያወደሙ ሲሆን፣ የእሳት አደጋ ተከላካዮች እሳቱን ለመቆጣጠር ከ120 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የመከላከያ መስመር ዘርግተዋል።

በኦሪገን ግዛት ደግሞ ሞቃታማና ደረቅ አየር እሳቱ ከ77.7 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ እንዲስፋፋ አድርጎታል። የእሳት አደጋ ተከላካዮች በ'ራይትስ ስፕሪንግ' እሳት ዙሪያ የመከላከያ መስመር ለማበጀት እየጣሩ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ጄሰን ኢንሳይን የተባለ የ47 ዓመት የቡልዶዘር ኦፕሬተር ህይወቱን አጥቷል። የቆርቆሮና ጣውላ ማምረቻ ኩባንያ ሰራተኛ የነበረው ይህ ግለሰብ አደጋው የደረሰበት ሐሙስ ዕለት እሳቱ በከፍተኛ ፍጥነት በመስፋፋቱ የማምለጫ መንገዱን ስለዘጋበት መሆኑ ተገልጿል።

ከአሜሪካ ድንበር በስተሰሜን በካናዳ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ግዛት፣ በፍጥነት እየተስፋፋ ካለው ሌላ ሰደድ እሳት ለማምለጥ ከ20,000 በላይ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል።

8 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.