Logo
Getu Temesgen
”ትውልድ ከእናንተ የሚፈልገው ሀገር እንጂ መንደር አይደለም!”
#ethiopia | በሀገራዊ ምክክር ልዩነቶች ተነሱ ብሎ “ቡራ ከረዩ” የሚሉ ሰዎች መስማት ያስገርማል፡፡ ለምክክር የተቀመጥነው የልዩነት ጉዳዮች ሰላሉን መስሎኝ፡፡ ዋናው ቁምነገር ልዩነት ለመፍታት የምንሄድበት መንገድ ነው፡፡ በዚህ የሀገራዊ ጉዳይ ተወያዮች ካልተቀራረቡ መሃል የሚባል መንገድ ከጠፋ ጉዳዩ ይደር ሊባል ይችላል፡፡ ባለበት ልንቀጥል የምንችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡

ጎበዝ ጉዳዩ ለሕዝብ ብይን ይቅርብ ለማለትም ጉዳዮ ግራ እና ቀኝ በደንብ እንዲበስል ማሳደር የብልህ ተግባር ነው፡፡ ዝርዝር ኪስ ይቀዳል- ይህ የአናሎግ ጊዜ ተረት ቢሆንም ጠቃሚ ነው፡፡ አሁን ክፍያ በሞባይል ነው፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እየተቃረበ መሆኑን ግን ተሳታፊዎች ይገባናል፡፡ ጠቅልሎ ለመውሰድም ሆኖ ሁሉን ሰጥቶ ባዶ አጭብጭቦ መውጣት የምክክር ተግባር ሊሆን አይችልም፡፡ አርቆ አጥሮ ግማሽ መንገድ ላይ ጥቅሜን አገኛለሁ የሚል የብልጣ ብልጥ አካሄደም ብዙ ሊያስኬድ አይችልም፡፡

ሁሉም በሚዛኑ ሀገር እንድታሸንፍ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ሀገር ስንል ኢትዮጵያ ማለታችን ነው፡፡ ሀገር ማለት ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የኢትዮጵያዊያን፣ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ሙስሊም ክርስቲያን እንዲሁም ሌሎች እምነቶች/አምልኮዎች፣ የተለያዩ ብሔረሰቦች፣ ውህድ የብሔር ማንነቶች፣ ወንድ ሴቶች፣ ከሕፃን እስከ አዋቂው፣ ወዘተ… ማለታችን ነው፡፡ ይህ ብዝሃ ማንነት ሊያስማማ የሚችል አማካኝ ፍለጋ የሚደረግ ጥረት ቀላል እንዳልሆነ የማይረዳ ቢኖር እርሱ ብዙ ይቀረዋል ብለን ማለፍ ብቻ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ ሲባል ከወጣነው ዳገት ከወረድነው ቁልቁለት በላይ ብዙ እንደሚቀር ቀሪውን ደግሞ እኔው እራሴ እወጣለሁ እወርዳለሁ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ወጣቶች ይህ የእናንተ ጊዜ ነው፡፡ ሀገር የእናንተ ለትውልድ የምታስተላልፉት ነው፡፡

ትውልድ ከእናንተ የሚፈልገው ምቾት ያለው ሕይወት ለመኖር የሚያስፈልገው ሀገር እንጂ፣ መንደር አይደለም፡፡ ዓለም ጠባ የዛሬ ኩነት በሰከንድ በሚሰማበት ጊዜ ወደኋላ መመልከት አይቻለም፡፡ ቢቻልም አያዋጣም፡፡

ለሀገር ግንባታ የሚያስፈልገው ጠጠር በቅንነት ለምታስቀምጡ ጀግኖች ሁሉ ምስጋና እና ክብር አለኝ፡፡

ከምክክር ሰፈር- ግርማ ሰይፉ

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.