Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ስፖርት) የአርጀንቲናው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ አባት እና ተጫዋቹ 14 ዓመት ከሞላው ጊዜ ጀምሮ ወኪሉ በመሆን ያገለገሉት ጆርጌ ሜሲ፣ ባደረባቸው የረጅም ጊዜ ህመም ምክንያት በ68 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ጆርጌ ቅዳሜ ማለዳ በትውልድ ከተማቸው ሮዛሪዮ (አርጀንቲና) በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ነው ህይወታቸው ያለፈው።

በዘንድሮው የክረምት የዓለም ዋንጫ ወቅት ስለ ጤንነታቸው የተለያዩ መላምቶች ሲነሱ የነበረ ሲሆን፣ የሜሲ ቤተሰብ አባላት አባታቸው "ከጤና ጋር የተያያዘ ሁኔታ" እያስተናገዱ መሆናቸውን ቢገልጹም የህመሙን አይነት ግን በሚስጥር ይዘውት ቆይተዋል።

ጆርጌ ልጃቸው በዓለም እግር ኳስ ታሪክ የምንግዜም ምርጡ ተጫዋች እንዲሆን በመቅረጽ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆን፣ ሜሲ በ2022 አርጀንቲናን እየመራ የዓለም ዋንጫን ሲያነሳ በኳታር ተገኝተው ተመልክተዋል። የአሁኑ የኢንተር ማያሚ አጥቂ ሜሲ ስምንት ጊዜ የባሎን ዶር አሸናፊ፣ በባርሴሎና አራት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን እና 10 የላ ሊጋ ክብሮችን ሲያሳካ አባቱ ሁሌም ከጎኑ ነበሩ።

ቤተሰቡ በየካቲት 2001 (እ.ኤ.አ) ሜሲ ገና የ13 ዓመት ታዳጊ እያለ ባርሴሎናን ሲቀላቀል ወደ ስፔን አቅንቶ ነበር። ምንም እንኳን የሜሲ እናት እና ሶስት እህት ወንድሞቹ ብዙም ሳይቆዩ ወደ ሮዛሪዮ ቢመለሱም፣ ጆርጌ ግን ከልጃቸው ጋር በባርሴሎና በመቆየት የቅርብ ድጋፍ ሲሰጡ ኖረዋል።

የሜሲ የልጅነት ክለብ የሆነው ኒዌልስ ኦልድ ቦይስ (Newell's Old Boys) ባወጣው የሀዘን መግለጫ ጆርጌን "ከባለቤታቸው ሴሊያ ኩቺቲኒ ጋር በመሆን የምንግዜም ምርጡን ተጫዋች ህይወት በራዕይ፣ በጥብቅ ዲስፕሊን እና በፍቅር የደገፉ ምሰሶ" ሲል አወድሷቸዋል። ክለቡ አክሎም፣ ማልቪናስ ከሚገኘው የወጣቶች አካዳሚ ጀምሮ እስከ ዓለም እግር ኳስ ክብር ጫፍ ድረስ ላደረጉት ያልተቋረጠ አጋርነት እና የጀርባ አመራር ምስጋናውን አቅርቧል።

የቀድሞ ክለቡ ባርሴሎና በበኩሉ ጆርጌ ለክለቡ ላሳዩት ቁርጠኝነት እና የልጃቸውን የሊዮን አስደሳች የእግር ኳስ ዘመን ለክለቡ አደራ በመስጠታቸው ምስጋና አቅርቧል። የአርጀንቲና እግር ኳስ ማህበርም "የአንበላችን እና አርማችን የሊዮኔል ሜሲ አባት ህልፈት በጥልቅ ያሳዝነናል" ሲል ሀዘኑን ገልጾ፣ በዚሁ ከባድ ጊዜ ከቤተሰቡ ጎን እንደሚቆም አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የአርጀንቲና የመክፈቻ ጨዋታ ላይ አንድ የአርጀንቲና ቴሌቪዥን አቅራቢ ጆርጌ ሞተዋል የሚል የሀሰት ዜና አሰራጭቶ እንደነበር ይታወሳል። አቅራቢው በኋላ ላይ ከስራው የለቀቀ ሲሆን፣ የሜሲ ቤተሰብ በወቅቱ ድርጊቱን "በጥብቅ የግል የቤተሰብ ጉዳይ ላይ የታየ የስሜት አልባነት እና የክብር እጦት" ሲል በጽኑ አውግዞት ነበር።

9 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.