Logo
EBC
ከኩርሙክ ወርቅ እስከ ዳንጎቴ ማዳበሪያ በማዕድን እና በግብርና የሚመራው የኢትዮጵያ አዲሱ የኢኮኖሚ ሽግግር
********************

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅሯን ለማዘመን እና የገቢ ምንጮቿን ለማስፋፋት የምታደርገው ጥረት በአሁኑ ወቅት አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

ኢትዮጵያ የምድር ውስጥ ሀብቷን በስፋት ማልማት ላይ ትኩረት ማድረጓን ተከትሎ፣ የማዕድን ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገቷ አዲስ የብርሃን ጭላንጭል እየሆነ መጥቷል።

በተለይም እንደ ኩርሙክ ያሉ ግዙፍ የማዕድን ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት መንገድ ከፍቷል።

በዚህም መሰረት ወርቅ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከሚላኩ ዋና ዋና የወጪ ንግድ ምርቶች አንዱ በመሆን፣ ከዚህ ቀደም ሙሉ በሙሉ በግብርና ምርቶች ላይ ተንጠልጥሎ የነበረውን የንግድ ሚዛን ማስተካከል አስችሏል።

በሌላ በኩል መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። ግብርና የሀገራችን ኢኮኖሚ ዋነኛ አከርካሪ እንደመሆኑ መጠን ሀገራችን በምግብ አቅርቦት በራስ እንድትተማመን ለማድረግ የታለሙ የካፒታል ኢንቨስትመንቶች እየተከናወኑ ነው።

በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚገነባው ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ የዚሁ ጥረት አካል እንደሆነ ይጠቀሳል። ይህ የአፍሪካው ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ሲገባ በዓመት 3 ሚሊዮን ቶን የዩሪያ ማዳበሪያ የማምረት አቅም ይኖረዋል።

ይህ ታሪካዊ እንቅስቃሴ ሀገራችን ለግብርና ግብአት ከውጭ ለማስገባት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት በእጅጉ ይረዳል።

ይህ እንቅስቃሴ የሀገራችንን የእርሻ ምርታማነት ከመጨመሩ ባሻገር፣ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተቀመጠ ትልቅ እቅድ ነው።

በኢንቲሃድ አብራር
#ethiopia #ebc #economicgrowth #miningindustry #agriculture #investment

8 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.