Logo
FastMereja
ጤና ልማትና ፀረ‐ወባ ማህበር በአማርኛ የተዘጋጀ የመጀመሪያውን የትምባሆ ቁጥጥር ዲጂታል ዳሽቦርድ ይፋ አደረገ!
#fastmereja :-በኢትዮጵያ በትምባሆ ቁጥጥር ዙሪያ ያሉ የተበታተኑ መረጃዎችን በአንድ ማዕከል ለማደራጀትና ተደራሽነታቸውን ለማስፋት ያለመው «የትምባሆ ቁጥጥርዳታ ኢኒሺዬቲቭ» (TCDI Ethiopia) ዳሽቦርድ፣ የአማርኛ ገጾቹን በይዘት በማበልፀግ በዛሬው ዕለት በይፋ ተመረቀ።

ይህ አገራዊ የዲጂታል ዳሽቦርድ ይፋ የተደረገው የጤና፣ ልማት እና ፀረ-ወባ ማህበር (HDAMA) ከኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ባለሥልጣን (EFDA) ጋር በመተባበር ባዘጋጁት ልዩ የመክፈቻ መርሃ-ግብር ላይ ነው፡፡

የዳሽቦርዱ በይፋ መከፈት በኢትዮጵያ የትምባሆ ቁጥጥር ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን እና ሕጋዊ ውሳኔዎችን ሙሉ በሙሉ በምርምርና በፅኑ መረጃ (Data-driven decision making) ላይ የተመሰረቱ ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተገልጿል።

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት እና ተመራማሪዎች ዘንድ ተበታትነው ይገኙ የነበሩ መረጃዎች በአንድ ቋት መደራጀታቸው፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ትክክለኛ አገራዊ ስታቲስቲክሶችን በመጠቀም ፈጣንና ውጤታማ እርምጃዎችን እንዲወስዱ እንደሚያስችላቸዉ ተገልጿል።

የቋንቋ ተደራሽነትና የባለድርሻ አካላት ምክክር የዳሽቦርዱ ገጾች በአማርኛ ቋንቋ ተበልፅገው መቅረባቸው የመረጃ ተደራሽነትን ከመጨመሩ ባለፈ፣ ለመገናኛ ብዙኃን፣ ለተመራማሪዎችና ለመላው ህብረተሰብ የግንዛቤ ማሳደጊያ ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ታውቋል።

በማስጀመርያ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የየዘርፉ ባለድርሻ አካላት የዳሽቦርዱን መመረቅ ተከትሎ በስፋት ዉይይት የተካሄደባቸዉ ሲሆን በውይይቱም ዳሽቦርዱ የሚያቀርባቸውን ዳታዎች ለሕግና ፖሊሲ ማሻሻያ አግባብነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አስተያየቶችን ተለዋውጠዋል።

ይህንን ጠቃሚ ዳሽቦርድ ወደ አማርኛ በመተርጎም፣ በማበልፀግ እና ለዛሬው ማስተዋወቂያ መድረክ የቴክኒክና የመረጃ ማዕከል ድጋፍ ላደረጉት የኢትዮጵያ የምግብ እና መድኃኒት ባለስልጣን፣ HDAMA፣ Development Gateway (DG) A Center for the Study of the Economies of Africa (CSEA) እንዲሁም ለሌሎች አጋር አካላት ምስጋና ቀርቧል።

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.