Logo
EBC
ለመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች አዲስ ተስፋን ይዘው የመጡት ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂዎች
**********************

የ3ዲ ኮንክሪት ሕትመት፣ ቀላል የዓረብ ብረት ግንባታ እና የኮንቴይነር መኖሪያ ቤቶች የዓለማችን የግንባታ ቴክኖሎጂ አዳዲስ ቋንቋዎች ሆነዋል።

እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በስፋት ጥቅም ላይ መዋል የጀመሩት በቅርብ ዓመታት ቢሆንም፣ በዓለም ዙሪያ በፍጥነት እየተስፋፉ ይገኛሉ።

እንደ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ እንግሊዝ፣ ኔዘርላንድስ እና ደቡብ ኮሪያ ያሉ ሀገራት የዜጎቻቸውን የቤት ፍላጎት በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመፍታት እነዚህን ቴክኖሎጂዎች ቀድመው ጥቅም ላይ ካዋሉ ግንባር ቀደም ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያም ፈጥናለች፣ ሀገራችን በእርግጥም ዘምናለች፤ ከሰሞኑ እነዚህን ሦስት የግንባታ ቴክኖሎጂዎች በማጣመር፣ የዜጎችን የቤት ጥያቄ ለመፍታት አንድ ብላ ጉዞ ጀምራለች!

በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እጅግ መሠረታዊ ከሆኑ ጥያቄዎች አንዱ ነው። የከተሞች መስፋፋት እና የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ይህን ፍላጎት ይበልጥ አንገብጋቢ አድርገውታል።

በተለይ በዋና ከተማችን አዲስ አበባ ያለው የቤት አቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም ለከፍተኛ የቤት ኪራይ ንረት እና ለኑሮ ውድነት ዋነኛ ምክንያት በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሔ ይሻል።

ይህን ችግር ለመፍታት መንግሥት ባወጣው የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ፣ 4.4 ሚሊዮን ቤቶችን በተለያዩ አማራጮች ለመገንባት አቅዷል። ይህንንም ለማሳካት፦

✅ የግል ዘርፉን ማሳተፍ፦ ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥትን ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ፣ የግል አልሚዎች በስፋት እንዲሳተፉ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች ተሻሽለዋል።

✅ የማኅበራት አደረጃጀት፦ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች ነዋሪዎች በማኅበር ተደራጅተው የቤት ችግራቸውን እንዲፈቱ የመሬት አቅርቦት እና መሰል ድጋፎች እየተደረጉ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም በተለመደው የቤት ግንባታ ሒደት ብቻ በከተሞች ያለውን የቤት አቅርቦት ችግር መፍታት ስለማይቻል፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

እነዚህ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በርከት ያለ ነው፦

👉 የ3ዲ ሕትመት (3D Printing)፦ ልዩ የሆነ ትልቅ ፕሪንተር በመጠቀም ኮንክሪት ወይም ሌሎች የግንባታ ቁሳቁሶችን በመደርደር ግድግዳዎችን እና መዋቅሮችን ይገነባል። ይህ ቴክኖሎጂ የብረት ግብዓትን እስከ 30 በመቶ፣ ሲሚንቶን ደግሞ ከ35 እስከ 40 በመቶ መቀነስ የሚችል ወጪ ቆጣቢ አማራጭ ነው። በአሁኑ ወቅት ባለ 4 ወለል (G+4) ቤቶች በዚህ ቴክኖሎጂ እየተገነቡ ሲሆን፣ ዲዛይኑ እስከ 14 ወለል እና ከዚያ በላይ የመገንባት አቅም አለው።

👉 ቀላል የአረብ ብረት ግንባታ፦ ቀላል እና ጠንካራ የብረት ክፍሎች በፋብሪካ ተዘጋጅተው ወደ ግንባታ ቦታ ተወስደው የሚገጣጠሙበት ዘዴ ነው። ይህም የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን የመቋቋም አቅም ያለው ሲሆን፣ ለፈጣን ግንባታ ምላሽ ከመስጠቱ ባሻገር ከእንጨት ይልቅ እጅግ ዘላቂ ነው።

👉 ተገጣጣሚ ቤቶች፦ የቅድመ-ፋብሪካ ቴክኖሎጂዎች የግንባታ ጊዜን በአጭሩ በመቅጨት ለፈጣን የቤት አቅርቦት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

መንግሥት እነዚህን ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጪ ቆጣቢ የሆኑ አዋጭ የግንባታ ዘዴዎች ወደ ተግባር እያስገባ ነው። ኢትዮጵያ በጀመረችው በዚህ የለውጥ ፍጥነት ጉዞዋን ስትቀጥል፣ ቴክኖሎጂው ደግሞ በበኩሉ ፈጥኖ ቤታችንን ይገነባልናል።

በዚህም በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ፣ የዘመናት የቤት ጥያቄያችን ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያገኝ ታላቅ ተስፋ ተጥሏል።

በዓይናለም ሀድራ
#ethiopia #ebc #housing #3dtechnology

29 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.