Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት (መብራት ኃይል) በኩል በቅርቡ በነዋሪዎች ላይ እየተጣለ ያለው አላግባብ የተጋነነ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ እና የቢሮክራሲ እንግልት ከፍተኛ ቅሬታን እያስነሳ ይገኛል። ለስምንት እና ዘጠኝ ዓመታት ያህል በመኖሪያ ቤታቸው ከ600 እስከ 700 ብር ብቻ መደበኛ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ይከፍሉ የነበሩ ነዋሪዎች፣ አሁን በድንገት ቤታቸው "ለቢሮ ወይም ለንግድ አገልግሎት የሚውል ነው" በሚል የተሳሳተ ምደባ እስከ 35,000 (ሰላሳ አምስት ሺህ) ብር እንዲከፍሉ እየተገደዱ መሆኑ ተጋልጧል። ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፣ ይህ የተቋሙ ድርጊት ዜጎችን ቃል በቃል "እያስጨለመ" ይገኛል።

ደንበኞች ይህንን የተጋነነ እና አቅም የማይፈቅደውን ክፍያ በመቃወም አቤቱታ ለማቅረብ ወደ መብራት ኃይል ቅርንጫፍ ቢሮዎች ሲያመሩ የሚጠብቃቸው ምላሽ እጅግ አሳዛኝ እና የኃላፊነት ስሜት የጎደለው ነው።

በቢሮዎቹ ውጭ በረዥም ሰልፍ የሚንገላቱት ደንበኞች፣ ብሶታቸውን በቅንነት የሚያዳምጥ አካል ከማጣትም አልፈው፣ "በቅድሚያ የተጠየቃችሁትን ክፈሉ፤ ቅሬታችሁ በሂደት ይስተካከልላችኋል" የሚል አስገዳጅ ምላሽ ከሰራተኞች እየተሰጣቸው ይገኛል። ይህን ያህል ግዙፍ መጠን ያለው ገንዘብ መክፈል ለማይችሉ ዜጎች ደግሞ "ካልከፈላችሁ መብራቱ ይቆረጣል" የሚል ዛቻ በግዴታ እየተጫነባቸው ነው።
ይህ አሰራር የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ብልሹነት እና የተጠያቂነት እጦት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

አንድን መኖሪያ ቤት ያለምንም ማጣራት ወደ ንግድ ወይም ቢሮ ታሪፍ ቀይሮ በአስር እጥፎች የጨመረ ክፍያ መጠየቅ፣ እንዲሁም "በቅድሚያ ክፈሉና በኋላ እናስተካክላለን" የሚለው አሰራር ዜጎችን ለከፋ የኢኮኖሚ እና ስነ-ልቦናዊ ጫና እየዳረገ ይገኛል። የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በዚህ ህዝብን እያስመረረ ባለው የመብራት ኃይል አሰራር ላይ በአስቸኳይ ጣልቃ ገብተው ማስተካከያ ካላደረጉ፣ ችግሩ የነዋሪውን የዕለት ተዕለት ህይወት ከማናጋት ባለፈ በመንግስት ተቋማት ላይ ያለውን አመኔታ በእጅጉ እንደሚሸረሽረው የጉዳዩ ታዛቢዎች ያስጠነቅቃሉ።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.