Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የደቡብ አፍሪካ መንግስት ጁን 30 መቃረቡን ተከትሎ የፀጥታ ሀይሉን ማጠናከሩን አስታወቀ፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ መጤ ጠል ቡድኖች ማንኛውም በአገሪቱ ውስጥ የሚገኝ ህገ ወጥ ስደተኛ እስከ ጁን 30 ለቆ እንዲወጣ ትእዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡ ከተቀመጠው ቀነ ገደብ በኋላ በአገሪቱ ውስጥ ከተገኘ ግን ንብረቱን እንደሚዘርፉና ህይወቱን እንደሚያጠፉ ጭምር ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ የደቡብ አፍሪካ መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ የፀጥታ ሀይሉን ለማጠናከር መወሰኑን አስታውቋል፡፡

የአገሪቱ ተጠባባቂ የፖሊስ ሚኒስትር ፊሮዝ ካቻሊያ ሲናገሩ ‹‹በሁሉም የአገራችን ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ ማህበረሰቦችን ፣ መሰረተ ልማቶችንና ቁልፍ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ለመጠበቅ አስፈላጊውን የተቀናጀ ሀይል የማስፈር እቅድ አለን›› ብለዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹ሰዎች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ የማሰማት መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ሽፋን ወንጀል መፈፀም፣ አመፅ ማስነሳትና ንብረትን ማውደም አይችሉም፡፡ እንዲህ አይነት ድርጊቶችን አንታገስም›› በማለት አስታውቀዋል፡፡ የ

ደቡብ አፍሪካ መከላከያ ሚኒስትር በበኩላቸው ከጁን 30 አንስቶ እንደአውሮፕላን ማረፊያ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችን ለመጠበቅ ወታደሮችን እንደሚያሰማሩ ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል የአገሪቱ ፍትህ ሚኒስትር ማሞሎኮ ኩባይ እስካሁን ድረስ አምስት ሺህ ህገ ወጥ የማላዊ ዜጎች ወደአገራቸው መሄዳቸውን ጠቅሰው በህገ ወጥ ስደተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ስልጣን ያለው መንግስት ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.