Logo
Getu Temesgen
የአብነት ትምህርት ቤቶች ትውልድን ከእሴት መውደቅ ለማዳን ወሳኝ ሚና አላቸው ተባለ
#ethiopia | ደብረ ሮሃ (ላሊበላ) – በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ የአራቱ ጉባኤያተ መጻሕፍት ትርጓሜ አዳሪ ትምህርት ቤት በበጎ አድራጊዎች ድጋፍ የተገነባው የማስፋፊያ ፕሮጀክት በብፁዓን አበው፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ምሁራን እና ሊቃውንት በተገኙበት በድምቀት ተመርቋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ምሁራን እንደገለጹት፣ በሀገሪቱ እየታየ ለሚገኘው የሥነ-ምግባር እና የትምህርት ውድቀት ዋነኛ መንስኤ የትምህርት ፖሊሲ ችግሮች ሲሆኑ፣ ትውልዱን ከአዘቅት ለማውጣት የሀገር በቀል እውቀት ማዕከላት የሆኑትን የአብነት ትምህርት ቤቶች ሚና በአግባቡ መገንዘብ እና በቅንጅት መደገፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በበኩላቸው፣ በተለያዩ ችግሮች የተፈተነችውን ሀገር ለማከም በትምህርት ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የወቅቱ ግዴታ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

በ1995 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ቄርሎስ መልካም ፈቃድ የተመሰረተው ይህ ጉባኤ ቤት፣ በርካታ ሊቃውንትን በማፍራት ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር አስተዋፅኦ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ታሪካዊ ሚናውን የሚመጥን የልኅቀትና የሊቃውንት ማዕከል ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑበት መሆኑ ተገልጿል።

ተቋሙን ወደ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ከማሳደግ ባለፈ፣ ዘመናዊ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል እና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶችን በማካተት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተግባራዊ ሥራዎች መጀመራቸውም ተጠቁሟል።

በመጨረሻም የጉባኤ ቤቱ መምህር ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አስናቀ ተቋሙን ለማደራጀትና ለማስፋፋት ላሳዩት ትጋት እውቅና ተሰጥቶታል፤ ለፕሮጀክቱ ድጋፍ ላደረጉ በጎ አድራጊዎችም ልዩ ምስጋና ቀርቧል።
#የአብነትትምህርት #ላሊበላ #የሀገርበቀልዕውቀት #ቤተክርስቲያን #ትምህርት #ethiopia

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.