Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በደቡብ አፍሪካ መጤ ጠል ተቃዋሚዎች ላይ ሽጉጥ ያወጣው ኢትዮጵያዊ ክስ ቀረበበት፡፡ በደቡብ አፍሪካ ዶክመንት የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች በሙሉ ከጁን 30 በፊት አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ ሰልፍ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ የተቃውሞ ሰልፍ እሁድ እለት በምፑዋላንጋ ግዛት በሚገኘው ዴልምስ ከተማ ተከናውኗል፡፡

በወቅቱም ወረደ ጂና ጉዬ የተባለ አንድ ኢትዮጵያዊ የሱቅ ባለቤት የአካባቢው ባለስልጣን በሆኑትና በሰልፉ ላይ ተሳታፊ በነበሩት ግለሰብ ላይ ሽጉጥ በማውጣት ማስፈራራቱ ተዘግቧል፡፡ ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያዊው ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ትላንት ፍርድ ቤት መቅረቡን ሲትዝን ጋዜጣ ገልጿል፡፡ ተከሳሹ ለፍርድ ቤቱ ድርጊቱን በመፈፀሙን አምኖ በስሜታዊነት እንዳደረገውና ከዚህ ቀደም ምንም አይነት ወንጀል ላይ እንዳልተሰማራ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም በዋስ ወጥቶ ለመከራከር እንዲፈቀድለት የጠየቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በዋስትናው ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኞ ቀጠሮ ሰጥቶታል፡፡

የክሱን ጉዳይ ለማየት ደግሞ መዝገቡን ለጁን 23 እንደቀጠረው ዘገባው አስረድቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ተቃውሞ ሰልፉን ከሚያስተባብሩት መካከል አንዱ የሆነው አክሽን ኤስኤ የተሰኘው የመጤ ጠል ድርጅት የኢትዮጵያዊውን ድርጊት አጥብቆ እንደሚቃወም አስታውቋል፡፡ የድርጅቱ መሪ የሆኑት ሜሪ ፋዲ ሲናገሩ ‹‹እንዲህ አይነቱን ድርጊት እንቃወማለን፡፡

የውጭ ዜጎች ወደአገራቸው ይሂዱ የምንለው ለዚህ ነው፡፡ መንግስት የውጭ ዜጎችን ፍልሰት መቆጣጠር ካለመቻሉም በላይ አሁን ደግሞ የውጭ ዜጎች የመንግስትን ስርአት መውደቅ እያሳዩን ነው›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የአፍሪካ ዲያስፖራ ፎረም ቃል አቀባይ ቦንጋኒ ምኳናንዚ ‹‹ማንም ሰው ቢሆን በአመፅ፣ በዛቻ፣ በማስፈራራትና በወንጀል ድርጊት ውስጥ ከተገኘ የሚወገዝ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ባህርይ በዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት የለውም፡፡›› በማለት ገልፀዋል፡፡

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.