ከፈተና ወደ ከፍታ፦ “ኢትዮጵያን ማንም አያሸንፍም” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል በተግባር ሲገለጥ
******************
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም “ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማንም አያሸንፍም” ማለታቸው ይታወሳል።
ይህ ታሪካዊ መልዕክት በወቅቱ ከነበረው ውስብስብ የጸጥታ እና የፖለቲካ ውጥረት አኳያ ስሜት ቀስቃሽ መፈክር አልነበረም፤ ይልቁንም ሀገራችን ፈተናዎችን በጽናት አልፋ ወደ ከፍታ የምታደርገውን ጉዞ ያበሰረ የተግባር ቃል እንጂ።
በወቅቱ በትግራይ ክልል ለሕግ ማስከበር እና ለመልሶ ማቋቋም ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት፣ እንዲሁም ከፍተኛ ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች የበረቱበት ጊዜ በመሆኑ፣ የሀገር ቀጣይነት ራሱ ትልቅ ጥያቄ ውስጥ የወደቀ መስሎ ነበር።
ይሁን እንጂ መፍረሷን የተመኙ ታሪካዊ ኃይሎች በየአቅጣጫው ቢሴሩም ያ የተስፋ ቃል ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም ግንባሮች ወደ ተጨባጭ ድል ተቀይሯል። ሀገራችን በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ እና በኢኮኖሚ ዘርፎች ታላላቅ ስኬቶችን በማስመዝገብ መዋቅራዊ ሽግግር እያደረገች ትገኛለች።
ፖለቲካዊ ሽግግር እና የሀገረ መንግሥት ግንባታ
በፖለቲካው መስክ ያጋጠሙ የውስጥ መከፋፈሎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ታሪካዊ እርምጃዎች ተወስደዋል።
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረውን ጦርነት በዘላቂነት ማስቆም የቻለ ሲሆን ኢትዮጵያ ‘የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሔ’ በሚለው መርህ ችግሯን መፍታት መቻሏን በተግባር ያረጋገጠችበት ነው።
በተጨማሪም የዘመናት የፖለቲካ ቁርሾዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰፊ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎችን አከናውኖ፣ ዋናውን ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ይገኛል። ይህም ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት የተጀመረውን የሽግግር ሂደት በተጨባጭ ያሳያል።
እነዚህ ተቋማዊ ግንባታዎችና የፀጥታ መዋቅር ማሻሻያዎች የሕዝብን አንድነት በማጠናከር የመከፋፈል አጀንዳዎችን ማክሸፍ ችለዋል።
የዲፕሎማሲ እና የሉዓላዊነት ድሎች
በዲፕሎማሲው መድረክ ኢትዮጵያ ያልተገቡ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን እና የተዛቡ ትርክቶችን በጥበብ በማለፍ ብሔራዊ ጥቅሟን አስከብራለች። እ.አ.አ በ2024 የብሪክስ (BRICS) ሙሉ አባል መሆኗ የሀገራችንን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል።
በሌላ በኩል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ ኃይል ማመንጨት የጀመረ ሲሆን በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው ይህ ፕሮጀክት ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ቀጣናዊ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን እያሳደገ ይገኛል።
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) በይፋ መጽደቁም የዘመናት የአንድ ወገን ተጠቃሚነት ታሪክን ወደ ፍትሐዊና የጋራ ተጠቃሚነት የለወጠ ታላቅ የዲፕሎማሲ ድል ተጠቃሽ ነው።
የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና አገራዊ ግስጋሴ
የሀገራችን ሁለንተናዊ አሸናፊነት በኢኮኖሚው ዘርፍም ጎልቶ ታይቷል። ተግባራዊ የተደረገው ሁለገብ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢንቨስትመንትን የሚስቡ ውጤታማ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ማክሮ-ኢኮኖሚውን አነቃቅቷል።
በጥቁር ገበያ ይባክን የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ወደ ሕጋዊ ሥርዓት በማስገባት፣ በታሪክ ከፍተኛ የተባለ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ላይ መድረስ ተችሏል።
በግብርናው ዘርፍ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የታየው መዋቅራዊ ሽግግር ሀገራችንን ከምግብ ጥገኝነት እያላቀቃት ሲሆን ምርቱ መጨመር ብቻ በዓመት ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ማዳን አስችሏል።
ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የከተማ ልማት እና አረንጓዴ አሻራ
ይህ ሁለንተናዊ መነቃቃት በታላላቅ ፕሮጀክቶችም በግልጽ እየታየ ይገኛል። በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን በቀጣዩ ሁለት ዓመታት ይህን ቁጥር 65 ቢሊዮን ለማድረስ እየተሠራ ነው።
በመዲናችን አዲስ አበባ የተጀመረው እና የዓለምን ትኩረት የሳበው የከተማ ኮሪደር ልማት በአሁኑ ወቅት ወደ 75 የሀገራችን ከተሞች በመስፋፋት ከተሜነትን እያዘመነ ይገኛል።
በእነዚህ ዓመታት የተለወጠችው አዲስ አበባ “ደህንነቷ አስተማማኝ አይደለም” በማለት ይቀርቡ የነበሩ አሉታዊ ትርክቶችን በማክሸፍ የዲፕሎማቶች እና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ተመራጭ መናኸሪያ ሆናለች።
በተጓዳኝም የአርሶ አደሩን ሕይወት የሚያዘምኑ የገጠር ኮሪደሮች እና ሞዴል መንደሮች ግንባታ ተጀምሯል። በመሰረተ ልማት ረገድ በ"ሚሽን 300" እና በ"አሰንት" ፕሮጀክቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አዲስ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታም በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል።
ምንም እንኳን ከቀድሞ የተወረሰ የዕዳ ጫና እና እንደ የዋጋ ንረት ያሉ ማኅበራዊ ፈተናዎች አሁንም ሙሉ በሙሉ ባይቀረፉም፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገቡት እነዚህ ታሪካዊ ስኬቶች የኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞ የማይቀለበስ መሆኑን የሚያረጋግጡ ሕያው ምስክሮች ናቸው።
ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያዊነትን ማንም አያሸንፍም” ሲሉ የተናገሩት ቃል መሬት የነካና በተጨባጭ መረጃዎች የተረጋገጠ አገራዊ ሀቅ መሆኑን ማየት እንችላለን።
ተግዳሮቶቻችንን ወደ ዕድል በመቀየር እነዚህን አበረታች ውጤቶች አጠናክረን በመቀጠል፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ የሁሉም ዜጋ ርብርብና ብሔራዊ መግባባት ወሳኝ ነው።
በለሚ ታደሰ
#ethiopia #resilience #economicgrowth #diplomacy #nationaldialogue #ebc

2 months ago