Logo
FastMereja
የሀዘን መግለጫ
የጤና ልማትና ፀረ-ወባ ማኅበር፤ የጥበብ ሰው፣ የህዝብ ድምፅ እና የለውጥ አጋራችን የነበረው ድምጻዊ ሰማኸኝ በለው በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ስንሰማ እጅግ ጥልቅ የሆነ ሀዘን ተሰምቶናል።

ድምጻዊ ሰማኸኝ በለው በሙዚቃ ስራዎቹ የሀገራችንን ባህልና እሴቶች በመጠበቅ ረገድ የማይረሳ አሻራ ጥሏል። ከጥበብ ስራው ጎን ለጎን ደግሞ፣ እንደ ማህበረሰብ የሚገጥሙንን የጤና ችግሮች በመቅረፍ ረገድ የነበረው አበርክቶ የሚዘነጋ አይደለም።

በተለይም ከጤና ልማትና ፀረ-ወባ ማኅበር ጋር በመተባበር፤ ድምጻዊት ቤተለሄም ዳኛቸው እና ትዕግስት መኮንን ጋር በመሆን በነጻ ያበረከቱት “እኛ ለእኛ” የተሰኘ ሙዚቃ፣ ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ የነበረው አስተዋጽኦ የላቀ ነበር።

በተጨማሪም፣ "ደቦት እንስራ" በሚለው እና በማህበረሰቡ ዘንድ "እያበል እያ እያ" በሚል በሚታወቀው ተወዳጅ ስራው እንዲሁም በሌሎች የቅስቀሳ ስራዎች፣ ማህበሩ የሚያከናውናቸውን የገቢ ማሰባሰቢያና የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎች በቅንነትና በታማኝነት በመምራት፣ ለብዙዎች ህይወት መትረፍ እና ለበሽታው ስርጭት መቀነስ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

እንደ ማኅበር፣ ለሰጠን የላቀ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እና ለነበረን የትብብር ዘመን ምስጋናችንን እያቀረብን፣ የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ እና ለመላው የጥበብ ቤተሰብ እንገልጻለን።

ለአርቲስቱ ነፍስ ዘላለማዊ እረፍትን፣ ለቤተሰቦቹና ለወዳጆቹ መጽናናትን እንመኛለን።
ጤና ልማትና ፀረ-ወባ ማኅበር

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.