Logo
EBC
በወዙና በደሙ ኢትዮጵያን ያፀና:- የጀግንነት አምባ
*****************

​"የኩሩ ህዝቦች መኖሪያ የህብረ ብሄር ቡቃያ፣ የሰላም ተምሳሌት ዓርማ የቀለሞች ህብር ኢትዮጵያ!"

ይህ የክብርና የሉዓላዊነት ብሔራዊ መዝሙር ስንኝ፣ ተራ የቃላት ድርደራ ሳይሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የታሪክ፣ የፅናትና የማንነት መልክ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ የህሊና ብሩህ መስታወት ነው።

​የመከላከያ ሰራዊቱ የማይበገር ጥንካሬ የሚመነጨው በልቡ ውስጥ ከነደደው የማያልቅ የሀገር ፍቅር እሳትና በውስጡ ከሰረጸው ጠንካራ ወታደራዊ ዲሲፕሊን ነው።

ሰራዊቱ ሀገርን በመጠበቅና ዳር ድንበርን በማስከበር ረገድ በዓለም መድረክ ላይ ተወዳዳሪ የሌለው፣ የታሪክን ታላላቅ ፈተናዎች በትከሻው የተሸከመ የሰላም ጽኑ ዐለት ነው።
የጦር ሜዳ ውሎው ስልታዊና አስፈሪ፣ የሰላም ጊዜው ደግሞ ለህዝብ አጋዥና መከታ ነው።

​ይህ ሰራዊት የሀገር ውስጥ ጋሻ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በአህጉሪቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ሁሉ ሰብአዊነትንና የህግ የበላይነትን ያስቀደመ፣ የሌሎችን ህዝቦች ነፃነትና ክብር እንደ ራሱ አድርጎ የጠበቀ እጅግ ተወዳጅና የተከበረ ኃይል ነው። በሊቤሪያ፣ በሩዋንዳ፣ በዳርፉርና በሶማሊያ በረሃዎች ውስጥ የፈሰሰው ላቡና ደሙ፣ የኢትዮጵያን ስም በዓለም የክብር መዝገብ ላይ በደመቀ ቀለም አስፍሮታል።

የሰራዊቱ አባላት ሌሎችን ማክበርና ለተቸገሩት መድረስ ከአባቶቻቸው የወረሱት የደም እሴት በመሆኑ, በተሰማራበት አህጉርና ቀጠና ሁሉ በህዝቦች ልብ ውስጥ የማይጠፋ የፍቅርና የታማኝነት አሻራ ጥሏል። በዚህም የተነሳ በአፍሪካ ምድር ህዝቦች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነው።

​ከዚህም በላይ፣ ይህ የጀግኖች ስብስብ ጠመንጃ ብቻ ሳይሆን አካፋና ዶማም መያዝ የሚችል የልማት ግንባር ቀደም ኃይል ነው። በኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ውስጥ፣ በታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብና በህዝባዊ አገልግሎቶች ላይ ቀዳሚ በመሆን ድህነትን የሚዋጋ፣ ህዝቡን ከረሃብና ከችግር የሚታደግ የላብ አርበኛ ነው።

ሰላምን በደሙ፣ ልማትንና ብልጽግናን ደግሞ በላቡ እያረጋገጠ የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን ያደርጋል። ይህ ሰራዊት በጦር ግንባር ጀግና፣ በልማት ግንባር ደግሞ መሀንዲስ ሆኖ ሀገርን ወደ ታላቅ ከፍታ ይመራታል።

​ባጠቃላይ፣ የኩሩ ህዝቦች መኖሪያ የሆነችውን ኢትዮጵያን እንደ አክሊል ደፍቶ፣ ቀለማቷን ጠብቆ፣ ታሪኳን አድሶ፣ ፈተናዎችን በብቃት ተሻግሮና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አግዞ የሚጓዘው የመከላከያ ሰራዊታችን፣ የኢትዮጵያ ህያው ህልውና፣ የነፃነቷ ዐለት፣ የብዝሃነቷ ውበት እና የነገው ታላቅነቷ እውነተኛ ዋስትና ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

Ethiopian Broadcasting Corporation #ጀግንነት #ኢትዮጵያ #ሰላም

2 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.