Logo
EBC
በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው የሰላም ስምምነት የመጨረሻ ውል ላይ ደረሰ
*************

በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚደረገው የሰላም ስምምነት የመጨረሻ ሰነድ መጽደቁን በሂደቱ ላይ ቁልፍ አስታራቂ የሆኑት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሸሪፍ አስታውቀዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጦርነት ለማቆም እና ወሳኙን የሆርሙዝ ወሽመጥ ድጋሚ ለመክፈት ያለመውን ይህንን ስምምነት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሰላም እንደ አሁኑ ቀርቦ አያውቅም” ብለዋል።

ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚነዙ የሀሰት መረጃዎችን ወደ ጎን በመተው ፓኪስታን ቀጣይ እርምጃዎችን ለማጠናቀቅ ከሁለቱም ወገኖች ጋር በቅርበት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጊቺም በበኩላቸው የጦርነቱ ማክተሚያ መቃረቡን አረጋግጠዋል።

ከሁለቱም ወገኖች ተስፋ ሰጪ መግለጫዎች ቢሰሙም፣ በአደባባይ ያላቸው የድርድር አቋም አሁንም የተራራቀ መሆኑ ይስተዋላል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን መገናኛ ብዙኃን የተናፈሰው የስምምነቱ ይዘት ከእውነታው የራቀ ነው ያሉ ሲሆን፣ ኢራናውያንን “በቅንነት ለመደራደር የማይመቹ” ሲሉ ተችተዋል።

በሌላ በኩል ኢራን አሜሪካ በዲፕሎማሲያዊ ሂደቱ ላይ በተደጋጋሚ ክህደት ፈጽማለች ስትል በመውቀስ፣ በዋሽንግተን ባህሪ ምክንያት የተገኘው መሻሻል ወደኋላ እየተመለሰ መሆኑን ገልጻለች።

ይሁን እንጂ ኢራን በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መደረሱንና በመጨረሻው የውስጥ ግምገማ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አስታውቃለች።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስምምነቱ በመጪው እሁድ መጀመሪያ ላይ ሊፈረም እንደሚችል የገለጹ ሲሆን፣ ቴህራን በበኩሏ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ጥርጣሬ ቢኖራትም ፊርማው “በሚቀጥሉት ቀናት” ሊከናወን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥታለች።

ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የሆርሙዝ ወሽመጥ ለሁሉም ክፍት እንደሚሆንና አሜሪካም በመጨረሻ የኢራንን የኑክሌር ቁሳቁስ እንደምታገኝ ተጠቅሷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኢራን ማንኛውም የተኩስ አቁም ስምምነት እስከ ሊባኖስ ድረስ መዘርጋት አለበት ብላ ብታስረግጥም፣ የእስራኤል ጦር ጥቃቱን በመቀጠሉ በደቡብ ሊባኖስ በርካታ ፍንዳታዎች እየተከሰቱ ይገኛሉ ሲሉ ዘ ቴሌግራፍ እና አልጀዚራ በዘገባቸው ጠቅሰዋል።

በመሐመድ ፊጣሞ
#usiranpeacetalks #straitofhormuz #middleeastpeace #ethiopianbroadcastingcorporation

3 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.