Logo
SeledaPost
በቲቤት ሰማይ ላይ የታየው አስደናቂውና አስፈሪው የደመቀ ቀይ ብርሃን

ከሰማይ ወደ መሬት ሳይሆን ከመሬት ወደ ጠፈር የሚተኮሰው ያልተለመደው መብረቅ።

ቲቤት በደቡብ ምዕራብ ቻይና የምትገኝ፣ ከኔፓል፣ ህንድ እና ቡታን ጋር የምትካለልና እጅግ ሰፊ በሆነው የኪንግሃይ-ቲቤት እምብርት ላይ ያለች ከፍተኛ ተራራማ ቀጠና ናት።

በአማካይ ከባህር ጠለል በላይ ከ4,000 እስከ 5,000 ሜትር ከፍታ ላይ በመገኘቷ "የዓለም ጣሪያ" (Roof of the World) በሚል ስያሜ ትታወቃለች።

በዚሁ ልዩ ስፍራ በቅርቡ በቲቤት ሻናን ክልል በሚገኘውና ከባህር ጠለል በላይ ከ5,000 ሜትር በላይ ከፍታ ባለው ፑማ ዩምኮ ሐይቅ (Lake Puma Yumco) አቅራቢያ በተከሰተ ኃይለኛ የነጎድጓድ ማዕበል ላይ እጅግ አስደናቂ እና አስፈሪ የሆነ የበራ ቀይ የብርሃን ምሰሶ ብልጭታ በቪዲዮ ተቀርጾ ወጥቷል።

የሳይንስ ልብ-ወለድ ፊልም የሚመስለውና "ሬድ ስፕራይትስ" (Red Sprites) በመባል የሚታወቀው ይህ ክስተት፣ ልክ እንደ ግዙፍ የባህር እንስሳ ቅርፅ ያላቸው የብርሃን ዘንጎች ወደ ጠፈር ሲዘረጉ ታይቷል።

ክስተቱን በከፍተኛ ጥራት የቀረጸው ዶንግ ሹቻንግ የተባለ የቻይና የሥነ-ፈለክ ተመራማሪና ፎቶግራፍ አንሺ ሲሆን፤ ክስተቱ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

ይህ ክስተት በተለምዶ እኛ ከምናየው መብረቅ እጅግ በጣም የተለየ ሲሆን የሚከሰተውም ከምድር ገጽ ከ50 እስከ 90 ኪሎ ሜትር ከፍታ ባለው የከባቢ አየር ክፍል ላይ ነው።

ከታች ባለው ደመና ውስጥ በጣም ኃይለኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ብልጭታ ሲከሰትና ከደመናው በላይ ባለው የላይኛው ከባቢ አየር ላይ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስክ ሲፈጥር የሚመጣ ነው ተብሏል።

Seledadotio
Seledadotio
2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.