Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በደርባን ከተማ ዶክመንት በሌላቸው ስደተኞች ላይ የአፈሳ ዘመቻ ተጀመረ፡፡ በደቡብ አፍሪካ ደርባን ሲቢዲ አካባቢ የመንግስት ሀይሎች ህጋዊ ዶክመንት በሌላቸው ስደተኞች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን አስታወቁ፡፡ በዚህ ዘመቻ የኢቲኪዊኒ ማዘጋጃ ቤት ከተለያዩ መንግስታዊ ኤጀንሲዎች ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በዛሬው እለት ብቻ 23 ዶክመንት የሌላቸው ስደተኞች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ከተያዙት ውስጥ ኢትዮጵያዊያን፣ ዚምባቡያዊያን፣ የማላዊ ዜጎችና ቻይናዊያን እንደሚገኙበት የከተማው ማዘጋጃ ቤት ገልጿል፡፡ በተጨማሪም በተደረገው ዘመቻ 5 ያህል በህገ ወጥ ስራዎች ላይ ተሰማርተው የተገኙ ሱቆች ላይ የማሸግ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡ ከታሸጉት ውስጥም በኢትዮጵያዊያን የሚተዳደሩ ሱቆች ይገኙበታል፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ በመግለጫው ‹‹እነዚህ ሱቆች የህገወጥ ስደተኞች መደበቂያ፣ ህጋዊ ያልሆነ አደንዛዥ እፅ መሸጫና የሴተኛ አዳሪነት ስራዎች ሲፈፀሙባቸው የነበሩ ናቸው›› ብሏል፡፡

የደቡብ አፍሪካ መንግስት ይህንን እርምጃ መውሰድ የጀመረው በአገሪቱ ውስጥ ስደተኛ ጠል ተቃውሞው እየተቀጣጠለ መምጣቱን ተከትሎ ነው፡፡ የአገሪቱ የፀጥታና የደህንነት መስሪያ ቤቶች ትላንት ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ ተቃውሞውን ለማብረድ በህገ ወጥ ስደተኞች ላይ የተቀናጀ እርምጃ እንዲወሰድ የሚል ውሳኔ ላይ የደረሱ ሲሆን ዛሬ በደርባን የተጀመረው አይነት እርምጃ በሌሎች ከተሞችም እንደሚቀጥል ከስፍራው የተሰራጩ መረጃዎች ገልፀዋል፡፡

10 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.