Logo
Getu Temesgen
በሀገር አቀፍ ደረጃ ራስን ማጥፋትን ለመግታት ያለመ የሦስት ወራት የንቅናቄ መርሃ ግብር ሊጀመር ነው
#ethiopia | በሀገራችን በተለይም በወጣቱ ማህበረሰብ ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ የመጣውንና አሳሳቢ ማህበራዊ ቀውስ እየሆነ ያለውን ራስን የማጥፋት ድርጊት ለመከላከል የሚያስችል አገር አቀፍ ንቅናቄ ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን ይፋ ሊደረግ መሆኑ ተጠቁሟል።

በሞቴ - ከመሞት መሰንበት በሚል መሪ ቃል ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት የሚቆየው ይህ የህይወት አድን ንቅናቄ በህብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙ ባህላዊ የመረዳዳት እሴቶችን እና የስነ-ልቦና ግንዛቤን በማሳደግ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ ከ720 ሺህ በላይ ሰዎች የራሳቸውን ህይወት የሚያጠፉ ሲሆን ይህም በዓለም ላይ ከሚሞቱ መቶ ሰዎች መካከል አንዱ ራሱን እንደሚያጠፋ ያመለክታል።

በተለይም እ.ኤ.አ በ2021 በተደረገ ጥናት ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ባሉ ወጣቶች ላይ ራስን ማጥፋት ዋነኛው የሞት መንስኤ ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህ ችግር በብዛት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት የሚከሰት ሲሆን በኢትዮጵያም በየዓመቱ ከ100 ሺህ ሰዎች ውስጥ 10 ያህሉ ራሳቸውን እንደሚያጠፉና ይህም ከጠቅላላው የህዝብ ቁጥር ጋር ሲሰላ በአመት ከ8 ሺህ እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች በዚሁ ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡ ከቀረቡት መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።

የአይሰለጥንብኝም ንቅናቄ ፕሬዝደንት መጋቢ ቢንያም አዱኛ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ለራስ ማጥፋት ድርጊት የአእምሮ ጤና እክሎች ዋነኛ መንስኤዎች ሲሆኑ የችግሩ መነሻዎች ደግሞ የሱስ ጥገኝነት፣ የደኅረ-ጕዳት መዘዞች፣ እንዲሁም ግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊ እና ማህበረሰባዊ ቀውሶች ናቸው።

ስትራቴጂው በዋናነት የሚያተኩረው የማህበረሰቡን ስነ-ልቦና መረዳት ላይ ሲሆን ሰዎች ችግር ሲገጥማቸው መጀመሪያ ወደ ባለሙያ ከመሄዳቸው በፊት በቤተሰብ፣ በጓደኞች እና በጎረቤቶች ዘንድ የመጀመሪያ ደረጃ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ይሰራል ብለዋል።

ለዚህም ሲባል ስልጠናውና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው ከባለሙያዎች ባለፈ በየቤቱ ባሉ እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶችና የመንደር መሪዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ችግሩን በቅድሚያ ለይተው ተገቢውን እገዛ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውንና በሞቴ ሲባል የተጠየቁትን የመስጠትና የመረዳዳት ጥልቅ ባህላዊ እሴትን መልሶ በማንቃት ትውልድን ከአስከፊ አደጋ ለመጠበቅ ታቅዷል።

ይህንን አገር አቀፍ እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ በየአካባቢው የሚገኙ 4,200 ማህበራትን በማንቃትና በማብቃት እያንዳንዱ ከ200 እስከ 300 የሚደርሱ አባወራዎችን ተደራሽ እንዲያደርጉ ይደረጋል።

ከዚህ ጎን ለጎን መልእክቱ ለታለመለት የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ለወጣቱ በፍጥነት እንዲደርስ የማህበራዊ ሚዲያ እና የዋና ዋና መገናኛ ብዙሃን ስትራቴጂዎች በጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን የስነ-ልቦና ምክር አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግም የቴክኖሎጂ እገዛ ስራ ላይ ይውላል።

ለውጡ በተከታታይ ስራ የሚመጣ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪዎቹ የፕሮጀክቱን ስኬታማነት ለማረጋገጥ በየወሩ ጠንካራ የክትትልና የግምገማ ስልት እንደሚዘረጋና በየደረጃው ያሉ አስተባባሪዎችም ግልጽ የሪፖርት አቀራረብ እንዲኖራቸው እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
#የአእምሮጤና #የህብረተሰብጤና #ንቅናቄ #ወጣቶች #ጤና #ኢትዮጵያ #getutemesgen #getu #ጌጡ #ጌጡተመስገን #addisababa

12 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.