Logo
YenetaTube
የፍቺ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ90 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ

በአዲስ አበባ ከተማ ፍቺ የሚፈጽሙ ባለትዳሮች ብዛት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ90 በመቶ በላይ ብልጫ ማሳየቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አስታውቋል።

ኤጀንሲው በተያዘው በጀት ዓመት 9 ወራት ብቻ 3 ሺህ 340 ፍቺዎች መመዝገባቸውን ይፋ አድርጓል። በጥቅሉ የጋብቻም ሆነ የፍቺ ምዝገባዎች ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸሩ ጭማሪ አሳይተዋል ተብሏል።

የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ ሹመይ፣ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ 8 ሺህ 315 ጋብቻዎች ተፈጽመዋልሰ ሲሉ ለአሐዱ ሬድዮ ብለዋል፡፡ የዚህ ዓመቱ የተጋቢዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል።

የሚፋቱ ባለትዳሮች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡ የተገለጸ ሲሆን፤ የተጠቀሰው አሐዝ በወሳኝ ኩነት በኩል ያልተከናወኑ ፍቺዎችን እንደማይጨምር የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡

ለፍቺ ምዝገባ ቁጥር መጨመር እንደ ምክንያት ተከጠቀሱት መካከል የኤጀንሲው የአገልግሎት አሰጣጥ መዘመን ይገኝበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በ11ዱም የምድብ ችሎት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ባሉበት ቦታ አገልግሎቱ መሰጠቱ ምዝገባው እንዲቀላጠፍና የተመዝጋቢዎች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የፍቺ ሥርዓት የሚመራው በተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 መሠረት ሲሆን፣ ፍቺ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ማለትም በባለቤቶቹ የጋራ ስምምነት ወይም በአንዳቸው አመልካችነት በፍርድ ቤት ውሳኔ እንደሚፈጸም ይታወቃል።

(አሐዱ ሬዲዮ)

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.