Logo
EBC
በጋራሙለታ እየለሙ ያሉ የግብርና ሥራዎች ለሀገራዊ የግብርና ሽግግር ተደማሪ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
*****************

ታሪክንና ውብ መልክዓ ተፈጥሮን የታደለው የጋራሙለታ አካባቢ፣ የኢትዮጵያን ሜዳና ተራሮች ምርት የሚታፈስባቸው የማድረግ ጉዞ ማሳያ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

አካባቢው በግብርና ልማት፣ በተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና በተፋሰስ ልማት ይበልጥ ወደተሻለ የልማት ከፍታ እየተሸጋገረ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሃረርጌ ዞን፣ በግራዋ ወረዳ ሜይራ ጉዲና ቀበሌ በመገኘት የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።

በጉብኝታቸውም የተመለከቱት የተፋሰስ ልማት ለአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ለምርትና ምርታማነት ማደግ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን አረጋግጠው፤ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው በተቀናጀ መልኩ እየለሙ የሚገኙ የፍራፍሬ፣ የደን ልማት እና አጠቃላይ የግብርና ሥራዎች ለሀገራዊ የግብርና ሽግግር ተደማሪ አቅም እየፈጠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የወረዳው አርሶ አደሮች በክላስተር በመደራጀት በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንስሳት ሀብት ልማት እና በንብ ማነብ ዘርፎች እያከናወኑት ያለው የተቀናጀ የግብርና ሥራ እጅግ የሚበረታታ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ገልጸዋል።

ይህ የተደራጀ የልማት እንቅስቃሴ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ሀገራዊ ንቅናቄን በስኬት ለማጠናቀቅ አጋዥና ከፍተኛ ሚና የሚኖረው መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ወደ አካባቢው በደረሱበት ወቅት ለተደረገላቸው ሞቅ ያለ አቀባበል እና ለተቸራቸው ሕዝባዊ አክብሮት ያላቸውን ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።
#ethiopianbroadcastingcorporation #ethiopia #temesgentiruneh #agriculturetransformation #garamuleta #clusterfarming

30 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.