Logo
FastMereja
"እማዬ የሁሉ እናት" በእናቶች ቀን እማዬን እናስታውስ
#fastmereja I የደጋግ እጆች መገለጫ፣ የመልካምነት ተምሳሌት፣ የአገር ወዳድነት አብነት፣ የሴቶች መቻል ማመሳከሪያ፣ የመልካም እናትነት ውል፣ የማሕበረሰብ ማስተሳሰሪያ ገመድ፣ የቢዝነስ ፈጠራ ሞዴል አማረች ዘለቀ ሸንቁጥ (ሴንተራል)።

የሆሳዕናው ሚካዔል በአክናፉ አጅቦ፣ ከፈጣሪ የተለገሰችውን አንዲት ሕፃን "እንካችሁ! ብሎ ለዝህች ቅድስት አገር አስረከበ፡፡ በሀድያ ዞን፣ ሆሳዕና ከተማ፣ በራሱ ስም በተሰየመለት አባባቢ (ሚካዔል ሰፈር)፣ በሰኔ 21 (ዕለተ-ማርያም) 1948 ዓ.ም. የበረከት ምሳሌ ናት፤ ሴት ስትወለድ፣ የፀጋ ማሳያናት፤ እንስት በቤተሰብ ስትበቅል። የኃላፊነት ቁነጮ ናት፤ እናት በማሕበረሰብ ውስጥ ስትገኝ። ይህንን ደስታ፣ ይንን ፍስሃ፣ ይህን ሃሴት፣ ሴትን የወለደ፣ ያሳደገ፣ አብሮ የኖረ፣ ጣዕሟን የተረዳ ያውቀዋል። በዚህ ቤተሰብ፣ በዚህ ቀዬ፣ በዚህ መንደር፣ አማረች የተባለች ሕፃን ስትወለድ የሆነውም ይህ እውነት፣ ይህ ደስታ፣ ይህ ፍንደቃ ነው። ማን ያውቃል፤ የህፃኗ መዳረሻ መልካም ገዶች ተገልፆላቸውስ ቢሆን!

ማንም ልጅ ሲወልድ ተስፋ ያደርጋል፤ ማንም ፍሬ ሲያገኝ ፈጣሪውን ያመሰግናል፤ ፍሬው በእግዚአብሔር መንገድ ሲፀድቅለት ደግሞ የበለጠ ልቡን በሀሴት ይሞላል። አድጎ ተመንድጎ፣ ተምሮ ሰርቶ፣ አግብቶ ወልዶ፣ የልፋት ጥሪቱን በሃብት፣ የሰው መሆን በረከቱን በልጅና ልጅ ልጆች፣ የሕዝብ ፍቅርን፣ ባለው ደግነትና ተግባቦት ሲታገዝ ምርጥ የቢዝነስ ፈጣሪ ደግሞ፣ ከሰውነት አልፎ አንድ ግለሰብ አገር ይሆናል፡፡ ባለታሪኳ በግል ተናጠል ከማውሳት ይልቅ፣ በአገርነት ቢነገርላቸው የሚያንስባቸው እንጂ፣ አይበዛባቸውም።

እኝህ የአገርነት ተምሳሌት የሆኑት እናት የሀዋሳዋ ወ/ሮ አማረች ሴንትራል ናቸው፡፡

በተወለዱበት ሆሳዕና ከተማ አድገው፣ መደበኛ ትምህርታቸውን በዛው ከተማ ተከታትለዋል፡፡ በለጋ እድሜ፣ ገና 14 ዓመት ሲሆናቸው፣ ትዳርን “ሀ” ብለው የሚቋደሱበትን ዕድል ሕይወት አዘጋጀችላቸው፡፡ በዚሁም፣ ነፍሳቸውን ፈጣሪ በአፀደ-ገነት ያቆይልንና፣ ለሻለቃ ወልደሰንበት ዘበርጋ ማሩ ለተባሉ ኩሩ ወታደር፣ በ1962 ዓ.ም. ተዳሩ፣ ፈጣሪም ትዳራቸውን ባርኮ፣ ኑሯቸውን ጎብኝቶ፣ የፍቅራቸውን ማሰሪያ አራት ወንድና አንድ ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡

የሰው ልጅ ቋሚ እግር እንጂ፣ ቋሚ አገር የለውም፤” እንደሚባለው፣ ከትዳር ምስረታ በኋላ፣ ከባለቤታቸው ሻምበል ወልደሰንበት ዘበርጋ በርካታ ክፍላተ-አገር ውስጥ ለመኖር ተገደዋል። ምክንያቱ ደግሞ ሻምበል ወልደሰንበት አገራቸውን የሚጠብቁ ቋሚ ቦታ ያልተወሰነላቸው ጀግና ወታደር በመሆናቸው ነው። በመሆኑም፣ በአዲስ አበባ፣ በአርሲ (አሰላ እና ጢቾ)፣ በጠረፍ አገር ሞያሌ፣ በመጨረሻም በሃዋሳ ከተማ በማድረግ አሳርገዋል።

ባላቤታቸው በግዳጅ ወደ ሰሜን ዕዝ በተላኩበት ግዜ፣ ወ/ሮ አማረች ቀደም ሲል ከእርሳቸው ጋር ሲኖሩ ከነበሩበት የፖሊስ ማሰልጠኛ ግቢ፣ ወደ ከፍተኛ 2 (በአሁኑ ሀይቅ ዳር ከ/ከተማ)፣ ቀበሌ 05 (አሁን ጉዱማሌ ቀበሌ) በመዛወር፣ በተሰጣቸው የቀበሌ ቤት ውስጥ በወር 24 ብር እየከፈሉ መኖር ጀመሩ።

በወታደራዊ ግዳጅ ላይ የነበሩት ጀግና ባለቤታቸው ሻምበል ወልደሰንበት ዘበርጋ በግንባር መሰዋታቸውን የተረዱት በዚሁ መኖሪያቸው ነበር። ከዚህ በኋላ፣ ልጆችን ለብቻ ማሳደግ፣ እነሱ የሰው እጅ እንዳያዩ ማድረግ፣ ጤንነታቸውን መንከባከብ፣ ማስተማርና ማብቃት የሚለው መራር እውነት እንደተጋፈጠባቸው ሲያረጋግጡ፤ ፈታኙን ሕይወት ፊት ለፊት ለመግጠም አልሰነፉም፤ ቆርጠው ተነሱ።

ይህንን ሕይወት መጋፈጥ በወቅቱ በቂ ዝግጅት ላላደረገች እንስት ምንያህል ፈታኝ እንደሚሆን መገንዘብ አይከብድም፤ በሆነው ከማዘን ይልቅ፣ የተሰበረን ልብ የሚጠግንና የሟችንም ሕልም የሚያሻግረው መፅናናት፣ መበርታት ጠንክሮ መስራት መሆኑን ያመኑት ወ/ሮ አማረች፣ በቀጥታ ያደረጉት እጃቸው ላይ ያለውን ጥበብ በመጠቀም ወደኑሮ መለወጥ ነበር።

ብዙዎች የወ/ሮ አማረችን ስም ሲጠሩ የወላጅ አባታቸውን ያህል የሚያስከትሉት መጠሪያ ነው "እሜዬ የሁሉ እናት" ይህ ልዩ መገለጫ የተሰጣቸው ልዩ በሆነ ስብዕናቸው ነው ። ያለ አንዳች ልዩነት፣ የሩቅ ሰው፣ የቅርብ ሳይሉ ሁሉንም እንደ እናት ስለሚወዱና ለሰው ያላቸው እውነተኛ ፍቅር ነው፡፡

ወ/ሮ አማረች በየዓመቱ 10 ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዘመዶቻቸውን እና ሌሎች ሰዎች የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ወጪ ችለው ያስተምራሉ፡፡ እስካሁን ከ300 በላይ ተማሪዎች ተመርቀው ወደ ስራ ተሰማርተዋል።

ወ/ሮ አማረች በየአመቱ የአካል ጉዳተኛ ለሆኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እና ህብረተሰብ የትምህርት ቁሳቁስ ወጪ ይሸፍናሉ።

በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ 5 ትምህርት ቤቶች በየአመቱ የተለያዩ በዓላትን በሚያከብሩበት ወቅት የመስተንግዶ ወጪ ይሸፍኑ ነበር።

ወላጅ አልባ ህፃናትን እና አረጋውያንን የመንከባከብ ስራ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች ድጋፍ ያደርጉ ነበር።

ይህ የተጠቀሰው ከብዙው በጥቂቱ ነው ። ወ/ሮ አማረች "እማዬ የሁሉ እናት" የተባሉበት መገለጫቸው ከዚህም በላይ ነው።

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.