Logo
EBC
የአፍሪካን ታሪክ በአዲስ መልክ እየጻፉ ያሉት የአህጉሪቱ ዲጂታል አምባሳደሮች
**************

በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ታሪክ የሚነገርበት መንገድ ከመደበኛው ሚዲያ ባለፈ በዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች (Content Creators) እጅ እየወደቀ ይገኛል።

በአህጉሪቱ መዲና አዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው የመጀመሪያው የአፍሪካ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ (ASMIS 2026) እንደሚያሳየው፣ እነዚህ ግለሰቦች ከዝና ባለፈ ለአህጉራዊ ገጽታ ግንባታ እና ለኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ነው።

በጉባኤው እየተሳተፉ ካሉ የአህጉሪቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መካከል የተወሰኑትን እናስተዋውቃችሁ፡-

አቤል ብርሃኑ በአፍሪካ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የጉዞ ቪሎገር (Travel Vlogger) ሲሆን፣ በቅርቡ በናይሮቢ በተካሄደው 'Africa Golden Awards 2026' የዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ የጉዞ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተብሎ ተሸልሟል። አቤል በአማርኛ ቋንቋ የሚያቀርባቸው ይዘቶች የሀገር ባህልን እና ዓለም አቀፋዊ እውነታዎችን በማገናኘት ረገድ ትልቅ አቅም አላቸው።

ዎዴ ማያ (Wode Maya) ጋናዊ የአፍሪካ ተቆርቋሪ ሲሆን፣ አፍሪካን "በተስፋ እና በኩራት" መነጽር ለዓለም በማሳየት ይታወቃል። አዲስ አበባን ለሥራው እንደ መነሻ (Launchpad) በመጠቀም የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴዎች፣ ዘመናዊ ከተሞች እና የኢንቨስትመንት አማራጮች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ተመልካቾቹ አሳይቷል። የእርሱ ይዘቶች የአህጉሪቱን አሉታዊ ገጽታ በመቀየር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝምን በማበረታታት ረገድ ቀዳሚ ናቸው።

ቪክቶር አዱዋ (Victor Adua) ናይጄሪያዊ ወጣት ነው። በቴክኖሎጂ እና ማርኬቲንግ ዘርፍ ወጣቶች እንዴት በዲጂታል ክህሎት ራሳቸውን መለወጥ እንደሚችሉ ያስተምራል። በተለይም በጊግ ኢኮኖሚ (Gig Economy) ላይ ያለው ልዩ ትኩረት ለኢትዮጵያ ዲጂታል ስትራቴጂ ጠቃሚ ትምህርት ይሰጣል።

ማጊ ሙኩታ (Maggie Mukuta) የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ተወላጅ ነች። በአፍሪካ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች እና በሴቶች የንግድ ተሳትፎ ላይ በማተኮር የአህጉሪቱን የፋሽን ኢንዱስትሪ ለዓለም ታስተዋውቃለች።

ወጣቶች ወደ ግብርና እንዲመለሱ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ እርሻ እንዲያካሂዱ የሚያነሳሱ ይዘቶችን የሚያቀርበው አፍሪካዊ ወጣት ደግሞ ኡጋንዳዊው ስቲቭ ካንባ (Steve Kamba) ነው።

እንደ ሄኒ የሻነው (Henny Yeshanew) እና ሸገር ዲጂታል (Sheger Digital) ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎችም በኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳደግ እና የሥራ ፈጠራን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት የራሳቸው አበርክቶ ይኖራቸዋል።

እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች ከመደበኛው ሚዲያ በበለጠ ወደ ወጣቱ የመድረስ አቅም አላቸው። እነዚህ ዲጂታል አምባሳደሮች ከማዝናናት ባለፈ የአፍሪካን እና የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲስ መልክ የመጻፍ (Narrative Transformation) ኃይል አላቸው።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

Ethiopian Broadcasting Corporation #africa #ethiopia #contentcreators #asmis2026 #narrativetransformation #ebc

28 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.