Logo
FastMereja
የሪል ስቴት ዘርፉን ለማስተካከል አቅጣጫ ተቀመጠ!
#fastmereja : የአፍሪካ ሪል ስቴት ማህበር (AFRES) የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ በዛሬዉ እለት አካሂዷል።

በጉባኤው ላይ በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት፣ የፖሊሲ ጥናቶችን ለማጠናከርና የአህጉራዊ ትስስርን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የፖሊሲ ጥናት፣ አድቮኬሲና የአባልነት ክፍል ሃላፊ አቶ ሲሳይ ዘነበ እንደገለጹት፤ ማህበሩ ከተመሰረተ አንድ ዓመት ቢሆነውም የዘርፉን እድገት የሚደግፉ የፖሊሲ ጥናቶችን በማከናወንና ከአስፈጻሚ አካላት ጋር በመወያየት መፍትሄዎችን በማመንጨት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በዛሬዉ እለት በተካሄደው የቀጠናዊ ጉባኤ በየዓመቱ በሴፕቴምበር ወር ለሚካሄደው ትልቅ አህጉራዊ ኮንፈረንስ እንደ መነሻ የሚያገለግል መሆኑን ገልፀዉ አልሚዎች ወደ ማህበሩ በመቀላቀል በዘርፉ ያሉ የህግ ማዕቀፍ ክፍተቶችን በጋራ እንዲያሻሽሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሀገሪቱ 3,000 የሚጠጉ አልሚዎች እንዳሉ ቢገመትም በማህበሩ የታቀፉት 100 አካባቢ ብቻ መሆናቸው ትልቅ ክፍተት መሆኑም ተጠቁሟል።

የአፍሪኮን ሪል ስቴት መስራችና የኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የቦርድ ሴክሬተሪ ጄነራል አቶ ዝናቡ ተበጀ በበኩላቸው፤ በዘርፉ ላይ አራት ዋና ዋና የችግር አይነቶችን የተለዩ ሲሆን እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ አዲሱ አዋጅ ሽያጭ በዝግ አካውንት (Block Account) በኩል እንዲከናወን የሚያዝዝ ሲሆን፣ ይህም አልሚዎች ስራቸውን በደረጃ እያከናወኑ ገንዘብ እንዲለቀቅላቸው በማድረግ የደንበኞችን ደህንነት እንደሚጠብቅ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት ያቀደች ሲሆን፣ ይህንን ግብ ለማሳካት ዘመናዊ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ወሳኝ መሆኑ በጉባኤው ላይ ታምኖበታል።

በተጨማሪም አዲሱ አዋጅ የውጭዜጎች በኢትዮጵያ ቤት መግዛት እንዲችሉ መፍቀዱ ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና ለኢንቨስትመንት እድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።

እንደ ቡርኪና ፋሶ ካሉ ሀገራት ጋር የሚደረገው የልምድ ልውውጥም ኢትዮጵያውያን አልሚዎች በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሄደው እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

በዛሬዉ እለት ከተካሄደዉ ኮንፈረንስ በተጨማሪ በዘርፉ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦች እና የሪል ስቴት አልሚዎች የምስጋና እና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

📷 ከበደ መክብብ

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.