Logo
FastMereja
አዲስ አበባን የአህጉሪቱ የሥነ-ፈጠራ ማዕከል የሚያደርገው ታላቁ ፌስቲቫል ይፋ ሆነ!
#fastmereja :"የሥነ-ፈጠራ ጥበባት ለለውጥ" በሚል መሪ ታላቁ የክራፍት አዲስ(CRAFT Addis 2026) ፌስቲቫል ከሚያዝያ 22 እስከ 24 ቀን 2018 ዓ.ም.ለሶስት ተከታታይ ቀናት በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እንደሚካሄድ በዛሬዉ እለት በተሰጠ መግለጫ ተገለፀ።

በዘሌማን (Zeleman) ኮሚኒኬሽን አዘጋጅነት ከአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን እና ፍሎዉለስ ኤቨንትስ ጋር በመተባበር የሚቀርበው ይህ መድረክ፤ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽንን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ንጉሥ ማልትን በአጋርነት ያሳተፈ ሲሆን፣ ዓላማውም የአፍሪካን የሥነ-ፈጠራ ኢንዱስትሪ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ አቅም መቀየር እንደሆነ ተገልጿል።

ዘሌማን በአፍሪካ የሥነ-ፈጠራ ዘርፍ ያለውን የ20 ዓመታት ልምድ በመጠቀም ያዘጋጀው ይህ ፌስቲቫል፣ ከመደበኛ ትርኢቶች ባለፈ የገበያ ተደራሽነት እና የቢዝነስ ትስስር ላይ ትኩረት እንደሚያረግ ነዉ የተገለፀዉ።

የዘሌማን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘላለም ወልደማርያም እንደገለጹት፣ “የክራፍት ዋነኛ ግብ የአፍሪካን የፈጠራ ምናብ ከተሰጥኦ ወደ ተቋም፣ ከሥነ-ፈጠራ ደግሞ ወደ ዘላቂ ብልጽግና የሚያሸጋግሩ የለውጥ መንገዶችን መገንባት ነው'' ብለዋል።

ፌስቲቫሉ ከ10,000 በላይ ተሳታፊዎችን በአካል፣ ከ3 እስከ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን ደግሞ በዲጂታል አማራጮች ተደራሽ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም አዲስ አበባን በአህጉሪቱ እያደገ የመጣው የሥነ-ፈጠራ ማዕከል የማድረግ ራዕይን እንደሚያሳካ ነዉ የተገለፀዉ።

የዘንድሮው ፌስቲቫል ልዩ ትኩረት የሚሰጠው የኢትዮ-ጃዝ አባት በሆኑት በክቡር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ ለሚቀርበው 'የክብርኮንሰርት' (Legacy Concert) ሲሆን ዶክተር ሙላቱ 10 አባላት ያሉትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆነውን የ'Steps Ahead' ባንዳቸውን ከለንደን በማምጣት ታሪካዊ የሙዚቃ ድግስ የሚያቀርቡ መሆኑም በመግለጫዉ ተገልጿል።

ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ መርሃ-ግብር ላይ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (Al)፣ በኢንቨስትመንት እና በሥነ-ፈጠራ ኢኮኖሚ ዙሪያ የፓናል ውይይቶች፣
በፋሽን፣ በፊልም፣ በዲጂታል ጥበባት (AR/VR) እና በቪዲዮ ጨዋታዎች (Gaming) ላይ ያተኮሩ ማስተር ክላሶች የሚቀርቡበት እንዲሁም ፈጣሪዎችን በቀጥታ ከገዢዎች ጋር የሚያገናኝ "የክራፍት ገበያ" ኤግዚቢሽን እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ፌስቲቫሉ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ የፈጠራ ባለሙያዎች እና በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መካከል ከ100 በላይ የንግድ ስምምነቶች እንዲፈረሙ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ሲሆን በተጨማሪም ባለሙያዎች ሥራቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያቀርቡ የሚያስችል የዲጂታል የሥራ ዕድል መድረክ(Digital Freelance Platform) ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

ዝግጅቱ በመጨረሻው ቀን የአዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻዎች እና የፈጠራ ማዕከላትን በሚያስጎበኝ ልዩ የከተማ ጉብኝት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ተነግሯል።

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.