Logo
YenetaTube
የቤላሩስ ፕሬዝዳንት ለሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ወዳጅነታቸውን የሚያጠናክር የጠመንጃ ስጦታ አበረከቱላቸው

የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ በፒዮንግያንግ የጓደኝነት ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት ለሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጠመንጃ በስጦታ ማበርከታቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ሁለቱም መሪዎች ሩሲያ በዩክሬን የምታካሂደው ጦርነት ቁልፍ ደጋፊዎች ሲሆኑ፤በቅርበት ለመተባበር እና ከምዕራባውያን የሚመጣባቸውን ጫና ለመቋቋም ተስማምተዋል።

የቤላሩስ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በለቀቁት ቪዲዮ፤ሉካሼንኮ ለኪም አውቶማቲክ ጠመንጃውን ሲያበረክቱ ‹‹ጠላቶች ቢመጡ በሚል ነው›› ሲሉ በቀልድ መልክ ተናግረዋል።

በምላሹም ኪም ለሉካሼንኮ ሰይፍ እና የቤላሩስ መሪ ምስል ያለበት የአበባ ማስቀመጫ በስጦታ ሰጥተዋል።

ሉካሼንኮ ለኪም እንደተናገሩት፤"እንደ ጓደኛ በዚህ ዓለም ውስጥ ሁሉንም ነገር እንዳየ ሰው ልነግርህ የምችለው ነገር ቢኖር፤ ይህንን ታታሪ እና ስነ-ስርዓት ያለው ህዝብ ይዘህ ሀገርህን ታላቅ ታደርጋታለህ " ማለታቸውን የቤላሩስ ዜና አገልግሎት ቤልታ ዘግቧል።

አክለውም "የዓለም አቀፍ ህግጋት በኃያላን መንግስታት በግልጽ ችላ በሚባሉበት እና በሚጣሱበት በዚህ ወቅት ሀገራት ሉዓላዊነታቸውን ለመጠበቅ እና የዜጎቻቸውን ደህንነት ለማሻሻል መተባበር አለባቸው ብለዋል።

ሉካሼንኮ የጓደኝነት ስምምነቱን ‹‹መሰረታዊ›› ሲሉ የገለጹት ሲሆን፤ኪም በበኩላቸው ስምምነቱ "የሁለትዮሽ ግንኙነቱ የተረጋጋ እድገት እንዲኖረው ዋስትና ይሰጣል" ማለታቸውን ቤልታ ዘግቧል።

በተጨማሪም ሁለቱ መሪዎች ከግብርና እስከ መረጃ ቴክኖሎጂ እና የህዝብ ጤና ባሉ ዘርፎች ላይ ለመተባበር ተስማምተዋል።

ሰሜን ኮሪያ እና ቤላሩስ በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሩሲያን በዩክሬን ጦርነት በመደገፋቸው በምዕራባውያን ከባድ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

በዚህ ወቅት ፒዮንግያንግ ለሩሲያ ጦር ወታደሮችን እያቀረበች ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት የምዕራባውያን ባለስልጣናት ለቢቢሲ እንደተናገሩት በዩክሬን ጦርነት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ 1 ሺህ የሚገመቱ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ተገድለዋል።

ዩክሬን በበኩሏ ሩሲያ በዩክሬን ኢላማዎች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የቤላሩስን ግዛት እንደ ጦር ሰፈር ትጠቀማለች ስትል ከሳለች።

ሀና ሰይፉ

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.