Logo
FastMereja
#ዘካተል ፊጥር

ዘካተል ፊጥር ከረመዷን ፆም መጠናቀቅ ጋር በተያያዘ ኃይማኖታዊ ግዴታ የሆነ የዘካ አይነት እንደሆነ የእስልምና አስተምሮ ያስረዳል።

ዘካ ድሆች በዒድ ዕለት ሰዎች ከመለመን እንዲድኑ፣ የዕለቱ ደስታ ተካፋይ እንዲሆኑና በፆም ወቅት ተከስተው ላለፉ አንዳንድ ጉድለቶች ማሟያ እንዲሆን ተብሎ የተደነገገ የኢባዳ አካል ነው።
#የዘካተል ፊጥር ምንነት

ሙስሊሞች ከዒድ አል ፊጥር በፊት ለችግረኞች የሚሰጡት የእህል /የምግብ/ ሶደቃ ነው።
#የዘካተል ፊጥር ሑክሙ፦
በሚችል ሰው ላይ ግዴታ ነው። [አልቡኻሪይ፡1503] [ሙስሊም፡ 984]
#ዘካተል ፊጥር በማን ላይ ነው ግዴታው?

በትንሽ በትልቁ፣ በሴት በወንዱ፣ የኢድ ፀሀይ ከመግባቷ በፊት የተወለደ ልጅ ሳይቀር ሙስሊም በሆኑ የቤተሰብ አባላት ቁጥር ልክ የሚወጣ ሶደቃ ነው።

ገና ያልተወለደ ፅንስ እዚህ ግዴታ ውስጥ አይገባም።

አንድ ሰው የሌሎችን ዘካተል ፊጥር (ለምሳሌ ከእሱ ጋር ያልሆኑ ቤተሰቦቹን ወይም የአገልጋዮችን) ማውጣት ይችላል። ግን እንደሚያወጣላቸው ማሳወቅ ይገባል።
#ዘካተል ፊጥር ግዴታ የሚሆነው?

ለእራሱም ለቤተሰቡም ለዒድ ሌሊትና ቀን የሚበቃ ቀለብ ባለው ላይ ሁሉ ግዴታ ነው። ድሃም ተቀብሎ ይሰጣል።
#ዘካተል ፊጥር ለማን ነው የሚሰጠው?
የዕለት ጉርስ ለሌለው ድሃ ኢድን ሳይቸገር እንዲያሳልፍ ።

ዘካ እና ዘካተል ፊጥር የሚሰጠው ለሙስሊም ብቻ ነው። ሌሎች ሶደቃዎችን ሙስሊም ላልሆኑ ወገኖች መስጠት ይቻላል።

ሑክሙን ባለማወቅ ወይም የሚገባውን አካል ስለማያገኙ ለሰራተኞቻቸው ዘካተል ፊጥር የሚሰጡ ሰዎች አሉ። ሰራተኞቻቸው የማይገባቸው ከሆኑ የተሰጣቸውን ለሚገባቸው አሳልፈው መስጠት ይኖርባቸዋል።
#ለዘካተል ፊጥር የሚሰጡ የእህል /የምግብ/ አይነቶች፦ ቴምር፣ ዘቢብ፣ አይቤ እንዲሁም በአካባቢው ለቀለብነት የሚውሉ፣ ረዘም ላለ ጊዜ ሳይበላሹ መቆየት የሚችሉ እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ ወዘተ. ያሉ የእህል /የምግብ/ አይነቶች ሁሉ ይገባሉ።

ምክንያቱም "ከምግብ አንድ ቁና" የሚል ሐዲሥ አለና። [አልቡኻሪይ፡ 1508] [ሙስሊም፡ 985] በዒዱ ዕለት መመገብ የሚችሉት አይነት ቢሆን ተመራጭ ነው።
#ዘካተል ፊጥርን በእራስ ፈቃደኝነት ጨምሮ መስጠት ይቻላል።

የሚስሰጠው መጠን በኪሎ ግራም:- በሐዲሥ የመጣው በስፍር ስለሆነ የክብደት መለኪያ ስንጠቀም እንደ እህሉ አይነት መጠኑ ይለያያል። ወደ ኪሎ ሲቀየር ዱቄት ላይ 2.5 ኪሎ አቅራቢያ ይመጣል። ይሄ የአንድ ሰው መጠን ነው። 10 ቤተሰብ ያለው ሰው 25 ኪሎ ማለት ነው።
#የዘካተል ፊጥር ጊዜው፦
ግዴታ የሚሆነው የረመዷን ወር የመጨረሻ እለት ተጠናቆ የዒዱ ሌሊት ሲገባ ነው። ልብ በሉ! በኢስላማዊው አቆጣጠር የአንድ እለት ቀዳሚው ክፍል ቀኑ ሳይሆን ሌሊቱ ነው።

ከዒድ ሶላት ማሳለፍ አይፈቀድም። ረስቶ በጊዜው ያላወጣ ሰው ሲያስታውስ ቢሰጥ ወንጀል አይኖርበትም። አውቆ ወይም ችላ ብሎ ወቅት ካሳለፈ ግን ወንጀል ላይ ወድቋል። ቢሆንም ግን የድሃ ሐቅ ስለሆነ ወቅቱ ቢያልፍም ሊያወጣ ይገባል። ሆኖም በፆሙ የሚደረግ ስለሆነ አይረሳም

አስቀድሞ መስጠት ይቻላል? ለሚሰበስቡ አካላት አንድ ቀን ሁለት ቀን ቀድሞ መስጠት ይቻላል። ከእዚህ ውጭ በጊዜው መስጠት እየተቻለ ቀደም ብሎ መስጠት አይገባም። ነገር ግን በዕለቱ ለመስጠት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲኖሩ ትንሽ ቀደም ብሎ መስጠት ይቻላል። እንዲሁም በውጭ ሃገራት ያሉ ሰዎች ለሚሰጥላቸው አካል ቀደም ብለው ገንዘቡን በመላክ እህሉን ማስገዛት ይችላሉ። ወኪሉ ግን በተቻለ መጠን ወቅቱን መጠበቅ አለበት።
#ዘካተል ፊጥር ከቤተሰብ እርቃችሁ ለምትገኙ ተማሪዎች ወላጆቻችሁ ዘካተል ፊጥር የማያወጡላችሁ ከሆነና የማውጣት አቅሙ ካላችሁ ዘካተል ፊጥር ማውጣት አለባቸው።
#ዘካተል ፊጥር አስገዳጅ ወይም አንገብጋቢ ሁኔታ ካልገጠመ በስተቀር ዘካተል ፊጥርን በገንዘብ ማውጣት አይቻልም።

የዒድ አልፈጥር እና የዘካተል ፊጥር ግንኙነት በእዚህ ልክ እንዲሆን የተደረገውም ሰዎች ከኢድ በፊት በሚሰጣቸው ስጦታ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ለማድረግ የሚያስችል የመረዳዳትና የማካፈል ኢስላማዊ አስተምሮ ነው።

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.