Logo
FastMereja
የአሜሪካ ዜግነት ላላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የቅጣት ምህረት ተደረገ
#fastmereja I የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈቀደላቸው የቆይታ ጊዜ በላይ (Overstay) ለቆዩ የአሜሪካ ዜግነት ላላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የቅጣት ምህረትና ቅናሽ ማድረጉን አስታወቀ።

ተቋሙ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ በኢሚግሬሽን ሕግ መሠረት የሚጣልባቸውን የገንዘብ መቀጫ ለመክፈል አቅም የሌላቸው ወገኖች ቅጣቱ እንዲነሳላቸው ሲያቀርቡ የነበረውን ተደጋጋሚ ጥያቄ መነሻ በማድረግ ውሳኔው ተላልፏል።

የውሳኔው ዝርዝር ነጥቦች፡-
1. ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት፡ የነበረባቸው ቅጣት ሙሉ በሙሉ ተነስቶላቸዋል። ያለ ምንም ቅጣት በቀጥታ ወደ ሕጋዊ የቪዛ አሠራር እንዲገቡ ይደረጋል።
2. ዕድሜያቸው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆኑ አዋቂዎች፡ የነበረባቸው የቅጣት ገንዘብ በግማሽ (50%) ቅናሽ ተደርጎላቸዋል። ቀሪውን ግማሽ በመክፈል ወደ ሕጋዊ የቪዛ አሠራር መመለስ ይችላሉ።

ይህ የምህረት እና የቅጣት ቅናሽ ዕድል የሚቆየው ለ60 ቀናት ብቻ ሲሆን፣ የሚተገበረውም ከመጋቢት 15/2018 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 15/2018 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

ተጠቃሚዎች በዚህ የ60 ቀናት የጊዜ ገደብ ውስጥ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና መሥሪያ ቤት በመቅረብ አስፈላጊውን ሰነድ በማሟላት እንዲስተናገዱ ጥሪ ቀርቧል። ይህ ዕድል ለአንድ ጊዜ ብቻ የተሰጠ መሆኑን የገለጸው ተቋሙ፣ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ በኋላ በሚቀርቡ ግለሰቦች ላይ ግን የተለመደው የኢሚግሬሽን ሕግና ደንብ ተፈጻሚ እንደሚሆን አሳስቧል።

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.