Logo
FastMereja
የሲዳማ የጊዜ አቆጣጠር ጥበብ...ይነበብ!!

የሲዳማ ዘመን አቆጣጠር መነሻው የፀሐይ፣ የጨረቃና ከዋክብት ሕግ በማጤን ላይ የተመሠረተ ነው። የሲዳማ ሀገረሰባዊ ዕውቀት ከዘመናዊ የሥነ ፈለክ (አስትሮኖሚ) ሕግጋት ጋር የሚገናኝ ነው። ያ አያንቶ (ባህላዊ አስትሮኖመር) የሰማይን ሚስጥር ያለ ቴሌስኮፕ በማጥናት ይሄንን ድንቅ ጥበብ እንዴት ለዚህ ትውልድ ማኖር ቻለ? የሚገርም ጥበብ ነው።

የሲዳማ የጊዜ አቆጣጠር ፀሐይንና ጨረቃን (Solar & Lunar Calander) መነሻ ያደረገ መሆኑን የወሥፉ አጥኚ መሠለ ካዳ "የሲዳማ ጊዜ አቆጣጠር" ለጊዜው ታትሞ ለገበያ ባልቀረበ መጽሐፉ ያትታል።

ሲዳማ የጨረቃ ካላንደር የሚጠቀመው የወቅቶችን መፈራረቅ ለመለየትና ለእርሻ ሥራ ነው። Badheessa, Hawado, Birra, Arro (በልግ፣ ክረምት፣ ፀደይ እና በጋ) የፀሐይ ካሌንደር ወቅቶች ናቸው።

በሲዳማ ማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው የጨረቃ ካሌንደር ነው። Lunar Calendar. ሲዳማ የጨረቃ ካሌንደር በሁለት ዓይነት አቆጣጠር እንደሚገለፅ ተመራማሪው መሠለ በግልጽ ያስቀምጠዋል። Siderial Lunar Cycle & Synodic Lunar Cycle.

Siderial Lunar Cycle (የአያንቶ ካሌንደር) ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ጨረቃ በምድር ዙሪያ የምታደርገውን ዑደት ከከዋክብቶችና ከሌሎች ፕላኔቶች አንፃር የሚቆጠር አቆጣጠር ነው። በሥነ ፈለክ ዘርፍ ጨረቃ መሬትን ዞራ ለመጨረስ 27/28 ቀናት እንደሚፈጅባት የሚታወቅ ሲሆን በሲዳማ አያንቶዎች ዘንድም 27/28 ቀኖች እንዳሉ ይታወቃል። እነኝ ቀናቶች ከመጀመሪያው ቀን Argaajjima ጀምሮ Bolla Bassa, Adula ama, Adula beetto....Bita... 28 (Lao) እየተባሉ የሚታወቁ ናቸው።

ሌላው የጨረቃ ካሌንደር Synodic Lunar Cycle (የፍቼ ጫምባላላ ካሌንደር) ተብሎ ይታወቃል። በዚህ ካሌንደር አቆጣጠር ሲዳማ የጨረቃ ቅርፅ (አዲስ ጨረቃ፣ ግማሽ ጨረቃ፣ ሙሉ ጨረቃ) ብቻ መሠረት በማድረግ ቀን የሚቆጥር ቀመር ሲሆን የፍቼ ጫምባላላ ቀን የሚውልበትን ዕለት የሚለይበት አቆጣጠር ነው።

በSynodic Lunar Cycle (Calandar) መሠረት 12 የጨረቃ ወራቶች የሚኖሩ ሲሆን ፍቼ ጫምባላላ የሚውለው በ12 የጨረቃ ወር በመጨረሻው ሳምንት፣ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ቃዋዶ ዕለት ሲሆን አሥራ ሶስተኛ ው አዲስ የጨረቃ ወር ከመጀመሩ በፊት ነው።

በአጠቃላይ የሲዳማ ህዝብ የጊዜ አቆጣጠር እጅግ የሚደንቅ የቀደምት አባቶች ጥበብ የሚገልፅ ሆኖ ብዙዎች ይሄንን ድንቅ ባህል ለማጥላላት ከጥንቆላ ወይም ከኮከብ ቆጠራ ጋር እንደሚያገናኙ ሳይሆን በሳይሳዊ ዕውቀት ማረጋገጥ የሚቻል መሆኑን ነው ተመራማሪው መሠለ ካዳ የሲዳማ አባቶች ዕውቀት ከሥነ ፈለክ (አስትሮኖሚ) ሳይንስ ጋር እያስተያዩ የሚገልፁት።
ይህ የሲዳማ ጊዜ አቆጣጠር መጽሐፍ ታትሞ በገበያ ላይ ሲውል ለአዲሱ ትውልድ ባህሉን እንዲያውቅ፣ እንዲጠብቅና እንዲያበለፅግ ትልቅ አቅም እንደሚሆነው እተማመናለሁ።

ሳሙኤል በላይነህ ቃ'ሜ
መጋቢት 4/2018 ዓ.ም
ሐዋሳ፣ ሲዳማ | ኢትዮጵያ 🇪🇹

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.