Logo
Getu Temesgen
♦️በናይጄሪያ ካላባር የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ንጋት ላይ ይገባል

♦️አትሌቶቹ ውጤታማ ቢሆኑም ሚኒማ ማሟላት አልቻሉም

♦️ቡድኑ ከ27 ሠዓታት በላይ በመጓዝ በጉዞ ተንገላቷል፤በመርከብ ሳይቀር ተጉዘው በቀጥታ ስታዲየም ገብተዋል

♦️እኩለሊት ተነስቶ ንጋት ላይ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል
#ethiopia | በቦትስዋና ጋቦሮኒ ከሜይ 2-3/2026 ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሪሌ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የሚረዳ ስዓት ለማስመዝገብ ወደ ናይጄሪያ ካላባር ተጉዞ የነበረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዛሬ ከእኩለ ሌሊት በኃላ ከሌጎስ ተነስቶ ንጋት ላይ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል ።

ቡድኑ በአሁን ሠዓት የውድድሩ ስፍራ ከነበረችው ካላባር ትናንት ወደ ሌጎስ በመምጣት ኤክሴል ሆቴል አርፈው ለጉዞ እየተዘጋጀ ሲሆን በናይጄሪያዊያን ሠዓት ዛሬ ምሽት 4:00 በኢትዮጵያ ሠዓት አቆጣጠር ደግሞ ከሌሊቱ 6:00 ከሌጎስ ተነስቶ 5:20 አካባቢ የሚጠጋ ሠዓት ከበረረ በኃላ ንጋት ላይ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

♦️ውጤታማ ቢሆኑም ሚኒማ ማሟላት አልቻሉም

የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ የልዑካን ቡድኑ ወደ ናይጄሪያ ካላባር የተጓዘው ከቦትስዋና 60ኛ ዓመት የነፃነት በዓል ጋር አብሮ በሚካሄደው የአለም አትሌቲክስ ሪሌ ውድድር ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ሚኒማ ለማሟላት ሲሆን አትሌቶቻችን በውድድሩ ውጤታማ ቢሆኑም፣ልምድ የሚያገኙበት ዕድል ቢመቻችላቸውም ቦትስዋና ለምታዘጋጀው የአለም ፈጣን እግሮች ትንቅንቅ መሳተፍ የሚያስችለውን ሚኒማ ግን አንዳቸውም ማስመዝገብ አልቻሉም።

የአጭር ርቀት ስፔሺያሊስቶችን የያዘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በካላባር በነበረው ቆይታ በ4X400 ሜትር ሪሌ በሴቶች 2ኛ ፣በወንዶች ደግሞ 3ኛ ደረጃን በአጠቃላይ በ400 ሜትር ወርቅ፣በ400 ሜትር ሴቶች ብር እና በ 400 ሜትር ወንዶች ነሃስ፣
በድብልቅ ሪሌ ውድድር አራተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ጥሩ በሚባል ደረጃ ቢያጠናቅቁም አንዳቸውም ለቦትስዋናው ጋቦሮኒ የሚያሳትፋቸውን ትኬት መቁረጥ የሚያስችል ሚኒማ ግን ማሟላት ሳይችሉ ነው ወደ አዲስ አበባ የሚመለሱት።

♦️ፌዴሬሽኑ ጥሩ ስራ ቢሠራም ከወቀሳ አይድንም

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በተለይ ፕሬዝዳንቱ ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በጀት ከመመደብ አንስቶ አትሌቶቹ ሚኒማ የሚያመጡበትን የናይጄሪያውን የውድድር እድል እንዲያገኙ ውድድሩን ከሚያዘጋጀው አካል ጋር ግንኙነት በመፍጠር ዕድሉ እንዲሳካ ያደረገው ጥረት በእጅጉ የሚያስመሠግነው ቢሆንም ነገሮች በጥድፊያ የተሞሉ መሆናቸው፣አትሌቶች በሆቴል ለአንድ ሳምንት እንኳን ተሠባስበው በቂ ልምምድ ሳያደርጉ ለአንድ ቀን ሆቴል ገብተው በነጋታው ለውድድር መጓዛቸው ፌዴሬሽኑን በተለይ ይሄን የማመቻቸት ኃላፊነት ያለበትን ፅ/ቤቱን ያስወቅሳል።

♦️ ከ27 ሠዓታት አድካሚ ጉዞ በኃላ ካላባር

ከሁሉም በላይ እጅግ አስገራሚው ነገር የልዑካን ቡድኑ ውድድሩ የሚካሄድባት ካላባር ለመድረስ ከ27 ሠዓታት በላይ የፈጀበት ከመሆኑም በላይ ከአውሮፕላን አድካሚ ጉዞ እንደገና የመርከብ አድካሚ ጉዞ አድርጎ ያለአንዳች እረፍት ከመርከብ ወደ ስታዲየም እንዲያመራ የተደረገበት መንገድ የፌዴሬሽኑን የጉዞ ዕቅድ ለትችት አሳልፎ የሚሠጥ ነው።

ሚኒማ ማምጣት ግቡና ዕቅዱ አድርጎ ወደ ናይጄሪያ የተጓዘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በፅ/ቤቱ አስቀድሞ የጉዞ ዝግጅት ባለማድረጉ ከአዲስ አበባ ሌጎስ፣ከሌጎስ ቀጥታ ወደ ካላባር ጉዞ ለማድረግ ዕቅድ ቢይዝም በዕለቱ ፍላይት(በረራ)የለም በመባሉ ቡድኑ ያለ ዕቅዱ ኦሮ የምትባል ትንሽ ከተማ ለማረፍ ተገዷል፤ከኦሮ ከተማ ወደ ካላባር ለመጓዝ በረራ ባለመኖሩ ቡድኑ እንደገና እንደቱሪስት አድካሚ የመርከብ ጉዞ አድርጎ ከመርከብ በቀጥታ ወደ ስታዲየም ለመግባት የተገደዱበት ሁኔታ እንደነበር ነው የካላባር የመረጃ ምንጮቻችን የገለፁልን፤በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የውድድሩ ስፍራ ከ27 ሠዓታት በላይ ጊዜን እንክት አድርጎ በመብላቱ የልዑካን ቡድኑን ለከፍተኛ ድካምና መንገላታት ዳርጎታል።

♦️የናይጄሪያዊው የቡድኑ ኮርዲኔተር ትልቅ ድጋፍ

ይህ አድካሚ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ እንዳይደገም ከፌዴሬሽኑ በላይ ጆን የሚባለው የናይጄሪያ ፌዴሬሽን ሠራተኛና የቡድኑ ኮርዲኔተር ትልቅ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ነው የሠማነው፤በእሱ ድጋፍም የነገ የርቀቱ የሀገር ተስፋ የሆነው የአትሌት መርዶኪዮስ ወልዴ የውድድር ቀንን በጉዞ በመንገላታቱ ምክንያት እስከማስቀየር የደረሠ ትልቅ ስራን የሠራ ሲሆን ቡድኑ ወደ ናይጄሪያ ሲጓዝ የገጠመው አይነት ረዥም ጉዞ አድርጎ እንዳይንገላታ በማሠብ ትናንት ከካላባር ተነስተው ወደ ሌጎስ ገብተው ደረጃውን በጠበቀው ኤክሴል ሆቴል እንዲያድሩና ዛሬ እኩለሊት ተነስተው ንጋት ላይ አዲስ አበባ እንዲገቡ ትልቅ ሚና በመጫወቱ ሁሉም የቡድኑ አባላት አመስግነውታል ናይጄሪያዊውን ጆንን።

♦️የጉዞ መንገላታት፣ከፍተኛ ሙቀትና ወበቅ፣የትራኩ ምቹ አለመሆን የሚኒማ እንቅፋት

የናይጄሪያው ውድድር በጉዞ መንገላታት፣በከፍተኛ ሙቀትና ወበቅ የታጀበ መሆኑ እንዲሁም ትራኩ የጭቃ ያህል የሚጣበቅና ለስፓይክ አመቺ ባለመሆኑ አትሌቶቻችን ያሠቡትን ያህል ውጤታማ እንዳይሆኑ የራሱን እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ነው መረዳት የቻለው።

ከዚህ ከጉዞ ጋር በተያያዘ ፌዴሬሽኑ አሁንም ከወቀሳ አልዳነም ለአትሌቶቹ ሚሊየን ብሮችን መድቦ ውድድሮችን አመቻችቶ መላኩ የሚያስመሠግነው ቢሆንም በቪዛ ጉዳይ ከአሜሪካው ችግር አሁንም እንዳልተማረበት ነው እየደረሱን ያሉት መረጃዎች የሚጠቁሙት።

ከናይጄሪያው የጉዞ ችግር በተጨማሪ በፖላንዱ ጉዞ የቪዛ ጉዳይ ዙሪያም መረጃዎች በስልክ እየደረሱን ነው፤ምንድነው የተፈጠረው?በቀጣይ ትክክለኛውን መረጃ አጠናክረን ለህዝብ የምናደርስ ይሆናል።

✍️✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)

👉ፎቶ ክሬዲት:የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.