Logo
FIDEL POST NEWS
የክብር ቀብር፦ በታምራት ደስታ "ከአንቺ አይበልጥም" ውስጥ በፍቅር ሰንሰለት የታሰረው የነፍስ ጩኸት

ለዚህ ዘፈን መነሻ ነው የተባለ ታሪክ ነው። ከሆነ አመት በፊት አንዲህ ሆነ። በአዲስ አበባ የሰው ድምፅ በሚበዛባቸው ምግብ ቤቶች መካከል አንድ የምግብና መጠጥ ቤት ባለቤት የሆነ ሰው፣ ሕይወቱንና ንብረቱን ብቻ ሳይሆን ክብሩንም ለሚስቱ አሳልፎ ሰጥቷል። ሚስቱ በሰው ፊት ስትጎነተል፣ ከሌሎች ጋር ስትላፋና እንዲያውም "እንሶላ ትጋፈፋለች" ተብሎ በሚወራበት ሁኔታ ውስጥ፣ እሱ ግን ምርጫው ሆዱ እያረረ ዝምታ ሆነ።

አንድ ቀን ሆድ ሲከፋው ተጣላት ። ግን ፍቅሯ አገረሸብኝ ብሎ በሽማግሌ ቢመልሳትም፣ ድርጊቷ አልታረመም። በመጨረሻም ይህ ሰው "ካንቺ አይበልጥም ክብሬ" ብሎ ራሱን ለውርደት አሳልፎ ሰጠ።

​ይህ ዝምታ ግን የትዕግስት ሳይሆን፣ የማንነት መፈራረስ ምልክት ነው። ታምራት ደስታ በዜማው እንዳቀነቀነው፣ ይህ ሰው ክብሩን እንደ አሮጌ ልብስ አውልቆ ጥሏል። ለምን? ምክንያቱም ከብቸኝነት ይልቅ ውርደት ይቀልለዋልና። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ትልቁ ፍርሃት "ብቻን መቅረት" ነው። ይህ ባል ሚስቱን ለብቻው ሳይሆን ከህዝብ ጋር ይጋራታል።

እሷ በሰው ፊት ክብሩን ስትገፈው፣ እሱ ግን ውስጡ እያረረ "ይሁን" ይላል። ይህ ውሳኔ ከፍቅር የሚመነጭ ሳይሆን፣ ራስን ካለመቀበል የሚመጣ የባርነት ጽዋ ነው። ራሱን እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ቁስ (Object) እየቆጠረ፣ የሰዎችን ትዝብትና ንቃትን ዋጥ አድርጎ ለመኖር መወሰኑ፣ የሰብአዊነቱ ማብቂያ ደወል ነው።

​ፈላስፎች "ገሃነም ማለት ሌሎች ሰዎች ናቸው" ይላሉ። ለዚህ ባል ግን፣ ገሃነም የሚስቱ መሄድ እንጂ የሰዎች ትዝብት አይደለም። በሰው ፊት ስትላፋ፣ ሌላው ሲዳብሳት እያየ "ክብሬን ተውት" አለ።

ለእሱ ገሃነም የሚጀምረው እሷ የቤትዋን በር ዘግታ ስትወጣ ነው። የሰዎች አይን እንደ ሾህ ቢወጋውም፣ የእሷ አለመኖር ግን እንደ ሞት ይከብደዋል። "ካንቺ አይበልጥም" የሚለው ቃል፣ የፍቅር መገለጫ ሳይሆን የነፍስ ባርነት መግለጫ ነው። ነፃነት የሌለው ፍቅር ደግሞ ፍቅር ሳይሆን እስራት ነው።

እዚህ ጋር ፍቅረኛው ወህኒ ቤት ሆናለች፣ እሱ ደግሞ በገዛ ፈቃዱ ቁልፉን የዋጠ ዘበኛ ነው።

​የናይጄሪያው ደራሲ ቺኑዋ አቼቤ በታላቅ ስራው Things Fall Apart ላይ፣ ወንድ ልጅ ክብሩ ሲነካ የሚሰማውን መርዶ ይገልጻል። በዚህ ግጥም ውስጥ ግን "ነገሮች አልተበተኑም" ። ይልቁንም በውርደት ውስጥ ተለጥፈው እንዲቆዩ ተደርጓል።

ባለታሪኩ የባህልን አጥር ሰብሮ፣ የወንድነትን ካባ አውልቆ፣ በባዶነቱ ፊት ቆሟል። "የት አባቱ ክብሬ" ሲል፣ የዘመናት ባህልንና የቤተሰብን ስም አቃጥሎ አመዱን ለንፋስ ሰጥቶታል።

አቼቤ እንደሚለው ባህል ሲፈርስ ህዝብ ይበተናል፤ እዚህ ግን ግለሰቡ ሲፈርስ ክብሩ ይበተናል። ይህ ሰው የቆመው በባዶ መሬት ላይ ሳይሆን፣ በራሱ ማንነት ፍርስራሽ ላይ ነው።

​ግጥሙ "የማየውና የምሰማው ክብሬን ይነካኛል" በማለት ይጀምራል። ይህ ማለት ሰውየው ድንዛዜ ውስጥ አይደለም፤ ህመሙ ይሰማዋል። የሚስቱ እጅ በሌላ ሰው ትከሻ ላይ ሲያርፍ፣ ልቡ እንደ መስታወት እንደሚሰበር ያውቃል። ነገር ግን ሰባሪዋን ሴት ከመጥላት ይልቅ፣ የተሰበረውን ማንነቱን ይዞ ሊለምናት ይመርጣል።

ይህ አስለቃሽ እውነት ነው—አንድ ሰው ራሱን ማክበር ሲያቅተው፣ የሚሰጠው ፍቅር ሁሉ የውርደት ውጤት ይሆናል። ሕመሙን እያወቀው ወደ ሕመሙ መሮጥ፣ የሥነ-ልቦና ራስን የማጥፋት ተግባር ነው።

እያንዳንዱ ስንኝ የልብ ትርታ ሳይሆን የቁስል አቃቂር ነው።
​ይህ ባል የቆሰለ ትዳሩን በውርደት ተሸክሞ በየቀኑ ወደ ምግብ ቤቱ ይሄዳል። ሚስቱ ስታዋርደው ድንጋዩ ይንከባለላል፤ እሱ ግን ደግሞ "ካንቺ አይበልጥም" እያለ ድንጋዩን ለመጫን ይሮጣል።

ይህ ትርጉም አልባ ህይወት በኢትዮጵያዊው ይሉኝታ ውስጥ ሲያልፍ፣ ታሪኩን እጅግ መራራ ያደርገዋል። የዚህ ሰው ድንጋይ የሚወደው ሰው ክህደት ነው። በየቀኑ የሚደገም ውርደት፣ በየቀኑ የሚታደስ መሸነፍ።

​"ፈጣሪዬ አቅሜን ያውቃል ላልችል አልሰጠኝም" የሚለው ስንኝ፣ የግጥሙ እጅግ ልብ ሰባሪ ክፍል ነው። እዚህ ጋር ግለሰቡ መለኮታዊ ኃይልን ለውርደቱ ምስክር ያደርገዋል።

እግዚአብሔር የሰጠው አቅም "ክፋትን የመቋቋም" ሳይሆን "ውርደትን የመቻል" ይመስል ይናገራል። ይህ የሀይማኖታዊ እይታ ስህተት ሳይሆን፣ የግለሰቡ ተስፋ መቁረጥ የመጨረሻ ደረጃ ነው። መሸከም የማይገባውን ቀንበር፣ የፈጣሪ ፈቃድ አድርጎ መውሰዱ የሞራል ሞቱን ያፋጥነዋል።

ፈጣሪ ነፃነትን ሰጥቶት ሳለ፣ እሱ ግን ባርነትን የፈጣሪ ስጦታ አድርጎ መቁጠሩ የነፍስ ጨለማ ነው።

​በናይጄሪያ ስነ-ጽሁፍ ውስጥ የሚታወቀው ወሌ ሶይንካ፣ "በአምባገነን ፊት ዝም የሚል ሰው በቁሙ የሞተ ነው" ይላል። እዚህ ጋር አምባገነኑ ፖለቲከኛ ሳይሆን "ፍቅር" ነው። ይህ ባል በፍቅር ስም የሚፈጸምበትን ግፍ ዝም ብሎ ሲቀበል፣ በቁሙ እየሞተ ያለ በድን ሆኗል።

"ሄደሽብኝ ከምሰቃይ ችላለሁ ቢያመኝም" የሚለው ቃል፣ በብቸኝነት ጨለማ ውስጥ ከመኖር፣ በውርደት ብርሃን ውስጥ መቃጠልን እንደሚመርጥ ያሳያል። ሞት አንድ ጊዜ ነው፤ ውርደት ግን በየቀኑ የሚሞቱት ሞት ነው። እሱ ግን የዘላለም ሞትን መርጧል።

​ግጥሙ "ክብሬን አይል ያፈቀረ የተሸነፈ ሰው" ሲል የሽንፈትን አዋጅ ያውጃል። ፍቅር ድል መሆን ነበረበት፤ እዚህ ግን ፍቅር መሸነፍ ሆኗል። "የተሸነፈ ሰው" ለራሱ የሚሆን ትርፍ የለውም።

ለራሱ የማይራራ ሰው፣ ለክብሩ አይቆምም። ይህ ስንኝ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንባ ያፈስሳል። ምክንያቱም ብዙዎች በዝምታ የሚሰቃዩበትን፣ ለፍቅር ሲሉ ማንነታቸውን ያጡበትን ድበቅ ህይወት ይገልጻልና። ሽንፈቱ ከሚስቱ ጋር ሳይሆን ከገዛ ራሱ ህሊና ጋር ነው። ራሱን ድል ያደረገ ሰው ብቻ ነው ለክብሩ የሚሞተው፤ እሱ ግን በራሱ ተሸንፏል።
​ታሪኩ በአዲስ አበባ ምግብ ቤት ውስጥ መከሰቱ፣ ማህበራዊ ትዝብቱን ያጠነክረዋል። ሰዎች "እንዴ ባሏን እንኳን አትፈራም?" ብለው ሲጠይቁ፣ መልሱ "ባሏ ራሱን አይፈራም" የሚል ነው። ራሱን የማያከብር ሰው፣ ሌላው እንዲያከብረው ሊጠይቅ አይችልም።

የሚስቱ ድፍረት የመነጨው ከእሱ ደካማነት ሳይሆን፣ እሷን ለማጣት ካለው ከፍተኛ ስጋት ነው። ይህ ስጋት ደግሞ እንደ ካንሰር ውስጡን እየበላው፣ የውጭውን ስሙን አርክሶታል።

​ "ካንቺ አይበልጥም ክብሬ ክብሬ" የሚለው መደምደሚያ፣ የአንድን ሰው ሙሉ በሙሉ መፈራረስ ያሳያል። ግጥሙ ሲያልቅ የሚቀረው ዜማ ሳይሆን፣ የክብር የቀብር ስነ-ስርዓት ነው።

በሞት የተለየን ታምራት ደስታ ይህንን ሲዘፍን፣ የአንድን ግለሰብ ታሪክ ሳይሆን፣ የብዙዎችን ስውር ስቃይ ነው ያወጣው። "ክብሬ" የሚለው ቃል ደጋግሞ ሲነሳ፣ ትርጉሙ እየጠፋ ይሄድና "ባዶነት" ብቻ ሆኖ ይረፋል።

ይህ ነው እንግዲህ ፍቅር ከክብር በላይ ሲሆን የሚመጣው አሳዛኝ ፍጻሜ። የሰው ልጅ ያለ ፍቅር ሊኖር ይችላል፣ ያለ ክብር ግን መኖር አይችልም—ቢኖርም ጥላ ሆኖ ነው።

​ፍቅር መስዋዕትነትን ይጠይቃል ይባላል፣ ነገር ግን መስዋዕቱ የሰውየው ክብር ሲሆን፣ መለኮታዊነቱ ቀርቶ ሰይጣናዊ እስራት ይሆናል።

ክብር አንዴ ከተቀበረ ትንሳኤ የለውም። ታሪኩም ሆነ ዜማው የሚያስተምሩን መራራ እውነት ቢኖር፡- ለሌላው ክብር ስንል የገዛ ክብራችንን የምንቀብር ከሆነ፣ የምንኖረው ሕይወት የራሳችን ሳይሆን የገዳያችን ነው የሚል ነው።
6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.