Logo
Getu Temesgen
የትዳር ፍቺ እና የፍቺ ውጤቶች
የተሻሻለው የቤተሰብ አዋጅ ቁጥር 213/1992

ጠበቃና የህግ አማካሪ ፋንታሁን ደለለው
0929101037,0983337690

መግቢያ #ethiopia | የዚህ ጽሁፍ ይዘት ፍቺ በምን አይነት መንገድ ሊፈጸም እንደሚችል እንዲሁም ፍቺ ሲፈጸም የፍቺ ህጋዊ ውጤቱ ምን እንደሆነና አሉታዊ ተጽእኖን በማስገንዘብ ከጋብቻ በፊት ቅድመ ግንዛቤ ተጋቢዎች እንዲኖራቸው የቀረበ የህግ ግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሁፍ ነው።

1. ፍቺ እንዴት ይፈጸማል?

ፍቺ በአራት አይነት መንገድ ወይም ምክንያት የሚፈጸም ሲሆን የመጀመሪያው በፍርድ ቤት ፍቺ ሲወሰን ነው። 2ኛው በሞት ከሁለት አንዳቸው ከዚህ አለም በሞት ሲለይ 3ኛው በፍርድ ቤት የመጥፋት ውሳኔ ሲሰጥ ሲሆን 4ኛው ጋብቻ ሲፈጸም መሟላት የሚገባቸው ነገር ሳይሟላ ሲቀር ነው።

1.1 ፍቺ በፍርድ ቤት

ባልና ሚስት በህጋዊ ጋብቻ ጸንተው እየኖሩ ከሁለት አንዳቸው ወይም ሁለቱ ፍቺን በፈለጉ ጊዜ በፍርድ ቤት በኩል የፍቺ ውሳኔ በመስጠት ይፋታሉ። አንቀጽ 81

1.2 ፍቺ በሞት

ከሁለት አንዳቸው በሞት በተለዩ ጊዜ ፍቺ እንደተደረገ ይቆጠራል። አንቀጽ 75
1.3 በፍርድ ቤት የመጥፋት ውሳኔ ሲሰጥ
ይህ የሚሆነው ከሁለት አንዳቸው አድራሻቸው ስላሉበት መረጃቸው የት እንዳሉ ሳይታወቁ ከሁለት አመት በላይ ሲቆዩ የመጥፋት ውሳኔ በመስጠት ትዳር የሚፈርስ ይሆናል።

1.4 ጋብቻ ሲፈጸም መሟላት ያለበት ሲጎል

ይህ ተጋቢዎች ጋብቻ ሲፈጽሙ መሟላት የሚገባው ሳይሟላ ቢቀር የሚፈርስ ይሆናል። በተሻሻለው ቤተሰብ ህግ ከአንቀጽ 6-16 ድረስ መሟላት ያለባቸው ነገሮች የተዘረዘሩ ሲሆን እነዚህ ካልተሟሉ የሚፈርስ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ለጋብቻ እድሜ ካልደረሰ፣ ያለተጋቢው ፍቃድ፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻ ጋብቻን የሚያፈርሱ ምክንያቶች ናቸው።

2. የፍቺ ሂደት በፍርድ ቤት

ፍቺ በአንድኛው ወገን ወይም በስምምነት ፍርድ ቤት በመምጣት የሚጠየቅ ነው። በአንድኛው ወገን ጠያቂነት ሲሆን ፍርድ ቤት ለማስማማት ብርቱ ጥረት የሚያደርግ ሲሆን ሁለቱን ለየብቻ ፣ አንድ ላይ በማድረግ ላለመግባባት መንስኤ የሆነውን ነገር ለይቶ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ያደርጋል።

ከሁለቱ ወገን ሽማግሌ አስታራቂ ወገን በመምረጥ በቂ የሽምግልና ጊዜ በመውሰድ እንዲታረቁ ጥረት ያደርጋል። በዚህ ወጤት አልስማማ ካሉ ቢቻል ድጋሚ በማነጋገር በቂ የማሰላሰያ ጊዜ ሰጥቶ በዚህም እንቢተኛ ከሆኑ የፍቺ ውሳኔ ይሰጣል። በስምምነት ከቀረቡ አጣርቶ መርምሮ ጠይቆ የሚያጸድቀው ይሆናል።

3. ፍቺ የሚያስከትለው ውጤት ምንድነው?

ከፍቺ በኋላ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች የሚከተሉ ሲሆን እኛ በዚህ ጹሁፍ የምንመለከተው የባልና ሚስት የንብረት ክፍፍል በተመለከተ ነው። አንቀጽ 83
ባልና ሚስቶች አብረው ያፈሩት ንብረቶች ካሉ እነዚህን ንብረቶች በአይነትም ሆነ በሽያጭ አድርገው እኩል የሚከፋፈሉት ይሆናል።

3.1 ንብረቱ የጋራ ወይም የግል መሆኑ እንዴት ይለያል?

ንብረቱ የግል ወይም የጋራ መሆኑ የሚታወቀው ባላቸው ማስረጃ፣በዚህ ቤተሰብ ህግ ፣ በስምምነት ሲሆን ያልተስማሙ ሆነው ከተገኙ በፍርድ ቤት በማስረጃ እና በህግ የሚለይ ይሆናል። የግል ሀብት አስቀድሞ ከጋብቻ በፊት የአንዳቸው ሆነ ከተገኘ የግል ሀብት ይሆናል። ነገር ግን አብረው በጋብቻ እያሉ የተፈራ ንብረት የጋራ ሆነው ይቆጠራል። በውርስ በስጦታ የተገኘ አስቀድሞ ከጋብቻ በፊት የነበሩ ሀብቶች የግል ሀብቶች ናቸው።
አንቀጽ 85፥86

3.2 የሶስተኛ ወገን እዳ፣ ገንዘብ እንዴት ይሆናል?

ይህ ንብረቱ ክፍፍል ከመደረጉ በፊት ከጋራ ንብረታቸው ላይ ተቀንሶ እዳም ሆነ የሶስተኛ ወገን ገንዘብ ለሶስተኛ ወገን የሚከፈል ይሆናል።

3.3 በክርክሩ ሂደት ንብረቱ የኔ ነው ባይ ሲመጣ መብቱ እንዴት ይከበራል?

ይህ ሰው ሲመጣ በፍ/ስ/ስ/ህግ ቁጥር 41 መሠረት የጣልቃገብ አቤቱታ ከማስረጃ ጭምር በማቅረብ የክርክሩ ተካፋይ ሆኖ በውሳኔው መሠረት የመብት ተጠቃሚ ይሆናል።
4. መንግስት፣ማህበራዊ ፣ የሀይማኖት ተቋማት ትዳርን ለመጠበቅ ምን ይጠበቅባቸዋል?

ጋብቻ በእዳንድ ምሁራን ዘንድ ተቋም የሚባል ሲሆን በአንዳንዶች ዘንድ ደግም የጋብቻ ውል ይባላል። ጋብቻ ተቋም ሲባል ልጆች፣አባት እናት ንብረት፣ቤት፣ተሽከርካረ ሌሎች የውልም ሆነ ከውል ውጭ ግንኙነቶች ጭምር የሚመሰረቱበት የራሱ የሆነ የጋብቻ ውል በህግ ያለው በህግ፣በመንግስት ፣በሀይማኖት በተለያየ ማህበራዊ ተቋም ህጋዊ እውቅና ያለው የማህበረሰብ እና የሀገር መሠረት ነው።

በትዳር ውስጥ የተሻሻለው የቤቸሰብ ህግ አንቀጽ 49 እንደሚያስቀምጠው ባልና ሚስት በመተማመን፣አብሮ በመኖር፣ በመከባበር በመተጋገዝ በመደጋገፍ መንፈስ መኖር እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ይህ ቤተሰባቸውን እና ከቤተሰቡ የሚገኘውን መልካም አጋጣሚዎች ለመጠበቅ ሲባል ነው።

ይህ ሲሆን በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩትን ተግዳሮቶችን በእኩል ግዴታ ለመወጣት ባልና ሚስት እኩል ግዴታ አለባቸው። ነገር ግን ግዴታን በመሸሽ መብትን ብቻ ለመጠቀም መፈለግ በባልና ሚስት መካከል መቃቃርን የሚያመጣ ነው።

ይህ እንዳይሆን የትዳር መልካም ፍሬዎችን ለመጠበቅ የመንግስት ማህበራዊ ተቋማት፣የሀይማኖትና ሌሎች የሚመለከታቸው የማህበራዊ ተቋሟት የህግ ግንዛቤ ማስጨበጫ አካላት ይህንን አጠቃላይ በትዳር ውስጥ የሚያጋጥሙ ተግዳሮትና መፍቴዎችን እንዲሁም መልካም በረከቶች ምን እንዴት እንደሆን አስቀድሞም ሆነ በትዳር ውስጥ እያሉ ሊያስገነዝቡ ያስፈልጋል።

ከዚህም አንጻር ሴቶችና ማህበራዊ ሚኒስተር ከጋብቻ በፊት ተጋቢዎች የትዳር ቅድመ ግንዛቤ እንዲኖር ማደረጉ በእጅጉ የሚበረታታ ነው።

5. የህግ ምክር

ተጋቢዎች ወደ ትዳር ከመግባታቸው በፊት የትዳር ምንነት፣በትዳር ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳዮችን፣እንዴት ተከባብረው ተማምነው መኖር እንዳለባቸው፥ ልጆቻቸውን ፣ንብረታቸውን እንዴት ማስተዳደር እንዳለባቸው ሀብት እንዴት በጋራ ማፍራት እንዳለባቸው በትዳር የማህበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዴት መሆን እንዳለባቸው አስቀድሞ በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው ያስፈልጋል።

https://www.facebook.com
https://t.me/Fantahunlawye...

6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.